ቀጥታ፡

የፍትሕ ሚኒስቴር እና የፖሊስ ተቋማት የምስክሮችንና የወንጀል ተጎጂዎችን አያያዝ ማሻሻል የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር ተፈራረሙ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 27/2015 (ኢዜአ) ፦ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የፖሊስ ተቋማት እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የምስክሮችና የወንጀል ተጎጂዎች አያያዝን ለማሻሻልና የማቆያ ማዕከላትን ማዘጋጀት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ፍቃዱ ጸጋ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግስቴ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ረዳት ኮሚሽነር ጸጋዬ ባልቻ እና ስድስት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ናቸው።

የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍቃዱ ጸጋ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ ምስክሮችና የወንጀል ተጎጂዎችን በወንጀል ፍትሕ ስርዓት ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥበቃ ማድረግና ማቆያ ማዘጋጀት የግድ የሚል መሆኑን አንስተዋል።


 

በዛሬው ስምምነት መሰረት በፍትሕ ሂደት ውስጥ በክርክር ወቅት እና ከፍርድ በኋላ ለተጎጂ ምስክሮች የሚሰጠው አያያዝና ድጋፍ ፍላጎትን መሰረት አድርጎ የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ምስክሮቹ በወንጀል ፈጻሚዎቹና በቤተሰቦቻቸው ብዙ የገንዘብ ማባበያ በማቅረብ እንዲሁም በማስፈራራትና በተለያዩ መንገዶች እንደሚደራደሯቸው ጠቅሰው፤ ስምምነቱ ይህን ተግባር የሚያስቀር መፍትሔ እንደሚያመጣ ጠቁመዋል።

ለአብነትም የምስክሮች ማቆያ መኖር ከተለያዩ አካላት ጋር ግንኙነት እንዳይኖራቸው በማድረግ በፍትሕ ሂደቱ ውስጥ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

እንዲሁም ስምምነቱ የወንጀል ምስክሮችን ማን እንደሚያገኛቸው፣ በምን ሁኔታ እንደሚያገኟቸው፣ ለመለየት እንደሚያግዝ አብራርተዋል።

ፍርድ ቤቶች በምስክሮች ያለመቅረብ ምክንያት በርካታ መዝገቦችን ሳያዩ የሚቀሩበት ሁኔታ እንዳለ በማንሳት የፍትሕ ስርዓቱን ከሚያግዙ ጉዳዮች መካከል የምስክሮች መኖር ወሳኝ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ባለ ድርሻ አካላት በዚህ በኩል በስምምነቱ መሰረት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት በመወጣት ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻል እንደሚገባቸው አሳስበዋል።


 

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግስቴ በበኩላቸው፣ ስምምነቱ የምስክሮችና የተጎጂዎች ጥበቃ ላይ የላቀ ውጤት ለማምጣት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

እንደ ህግ አስከባሪ ተቋም የማቆያ ስፍራን በማዘጋጀት በኩል እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ ስምምነት ለህግ ማስከበር ስራዎች መሳካት የላቀ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።

በተለይ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና በሰዎች መነገድ ላይ ከፍተኛ የሆነ ካፒታል የሚዘዋወርበትና አደገኛ ወንጀለኞች ያሉበት መሆኑን በማንሳት፤ የምስክሮች ማቆያ መኖር ጠንካራ እርምጃ በመውሰድ አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም