ቀጥታ፡

የመደመር እሳቤ አገር በቀል እውቀቶችን መሰረት በማድረግ ፈተናዎችን ተቋቁሞ አገርን የሚያሻግሩ የልማት ስራዎች እንዲከናወኑ አስችሏል- ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች

አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 27/2015(ኢዜአ):- "የመደመር እሳቤ አገር በቀል እውቀቶችን መሰረት በማድረግ ፈተናዎችን ተቋቁሞ አገርን የሚያሻግሩ የልማት ስራዎች እንዲከናወኑ አስችሏል" ሲሉ ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ”መደመር ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ አገር አቀፍ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

በውይይት መድረኩ ላይ ምክትል አፈ-ጉባኤዋን ጨምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትር አዲሱ አረጋና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡

በመድረኩም "የመደመር እሳቤ ከአገር በቀል እውቀቶች ጋር ያለው ትስስር እና ለተቋማት ግንባታ ያለው ሚና" ፣ "መደመርና ሜጋ ፕሮጀክቶች" እንዲሁም "የመደመር ቀጣይ እድሎችና ፈተናዎች" ላይ ትኩረት ያደረጉ የውይይት መነሻ ጽሁፎች ቀርበዋል።

የሕግ ምሁሩ ዶክተር ሮባ ጴጥሮስ ኢትዮጵያ በሕዝቦች መካከል አብሮነትና ሰላምን የሚያሰርጹ በርካታ የአገር በቀል እውቀቶች ባለቤት ናት ብለዋል።

ከዚህ አኳያ "መደመር" የኢትዮጵያዊያን የልቦና ውቅር የሆኑ አገር በቀል እሴቶችን መሰረት ያደረገ እሳቤ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የመደመር እሳቤ በተለይ ለመጻኢ የኢትዮጵያ ጉዞ ቀልፍ መሰረት የሆኑትን ሰላምና አብሮነት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

ከዚህ አኳያ ስልጣንን በኃይል ለመቆጣጠር እንዲሁም ጥላቻና መከፋፈልን በብዕር ለማስፋት የሚደረግ ጥረት ሊቆም ይገባል ብለዋል፡፡


 

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት ቅድሚያ ሰጥቶ ከሰራባቸው ጉዳዮች ዋነኛው የተቋማት ግንባታ መሆኑን አንስተዋል፡፡ 

በዚህ ረገድ በጸጥታና ደህንነት ተቋማት የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎችን ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ተቋማቱ ባለፉት አምስት ዓመታት የገጠሙ ፈተናዎችን በመቋቋም የኢትዮጵያ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ በሆነ መልኩና ሙያን መሰረት በማድረግ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል ነው ያሉት።

ዛሬን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን መጻኢ ጉዞ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተቋማቱ መገንባታቸውንም ገልጸዋል።  

የመደመር ዕሳቤ የሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ለማክሮ- ኢኮኖሚ ግንባታ መሰረት የጣለ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ነመራ ገበየሁ ናቸው።


 

ከአገራዊ ለውጡ በፊት ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በአግባቡ የማስተዳደር አቅም ማነስ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከበጀቷ 15 በመቶ የሚሆነውን ገንዘብ ስታጣ መቆየቷን አውስተዋል። 

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት በመደመር እሳቤ ማዕቀፍ ውስጥ ባከናወነው የኢኮኖሚ ሪፎርም የሜጋ ፕሮጀክቶችን የአስተዳደር ችግር ከመቅረፍ ባሻገር ብዝሃ-ኢኮኖሚ ዘርፍ መገንባት ተችሏል ነው ያሉት፡፡

ለአብነትም በቱሪዝም፣ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂና ኮሜርሻል ግብርና ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ስራ ተከናውኗል ሲሉም ገልጸዋል።

በተለይ በቱሪዝም ዘርፍ አዲስ መነቃቃት እየተፈጠረ መሆኑንም በማንሳት።


 

የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካና ርዕዮተ-ዓለም ዘርፍ ኃላፊ ዛዲግ አብርሃ፤ "መደመር የማያቋርጥ እድገት ያለው እና አዲስ ሃሳብ፣ አዲስ መንገድ እና አዲስ ባህል የያዘ እሳቤ ነው" ብለዋል።

የሃሳብ ግልጽነት፣ ብሔራዊ መግባባት፣ አገራዊ ምክክር፣ ለድርድርና ሰላም ዕድል መፍጠር የመደመር እሳቤ ተስፋዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል። 

ለአዲስ የፖለቲካ ባህል መሰረት መጣልና ሃሳብ ዋጋ እንዲያገኝ ማድረግም ሌላኛው የመደመር ተስፋ መሆኑን ጠቁመዋል።

ካልተቋጨ የአገረ መንግስት ግንባታ ጋር ተያይዞ ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችም የእሳቤው ቀጣይ ፈተናዎች ናቸው ነው ያሉት።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም