የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በትግራይ ክልል ከ7 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የልማትና የስራ አመራር ስልጠና መስጠቱን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በትግራይ ክልል ከ7 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የልማትና የስራ አመራር ስልጠና መስጠቱን ገለጸ
መቀሌ ፤ ሃምሌ 27 / 2015 (ኢዜአ) ፡-የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በትግራይ ክልል ከ7 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የልማትና የስራ አመራር ስልጠና መስጠቱን አስታወቀ።
በባንኩ የመቀሌ ዲስትሪክት ስራ አስኪያጅ አቶ ዮሃንስ አማረ ለኢዜአ እንደገለፁት ባንኩ በመቀሌና በማይጨው ከተሞች ለአምስት ቀን ስልጠና ከሰጣቸው ወጣቶች መካከል 30 በመቶዎቹ ሴቶች ናቸው ።
ስልጠናው የልማት ፕሮጀክት ቀረፃና አተገባበር፣ የፋይናንስ አያያዝ፣ የሰራተኛ አስተዳደር፣ ኢንተርፕሪነርና ፋይዳው፣ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ስራ ውጤት በሚሉ ርእሶች ላይ ያተኮረ መሆኑን ተናግረዋል ።
ስልጠናው ወጣቶቹ በግልና በሽርክና በመስራት ውጤታማ ለመሆን አቅም የሚፈጥርላቸው መሆኑን ተናግረዋል ።
በንግድና ሌሎች የገቢ ማስገኛ ስራዎች ለመሰማራት በእውቀት ላይ የተመሰረተ ፕሮጀክት ለሚያዘጋጁ በአይነት የብድር አቅርቦት እንደሚያደርግላቸው አመላክተዋል።
“ይኽውም ባንኩ ለልማትና ለንግድ እንቅስቃሴ የሚያስፈልጉ የተለያዩ ማሽነሪዎችና እቃዎችን ከአገር ውስጥና ከውጭ ገዝቶ በብድር የሚያቀርብላቸው ይሆናል” ሲሉ ገልጸዋል ።
ተቀባይነት ያላቸው ፕሮጀክቶች አቅርበው ለፀደቀላቸው በግልና በሽርክና ለሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ማህበራት ለማሽነሪዎች ግዥ በባንኩ ወጭ እንደሚደረግ ጨምረው አብራርተዋል።
ስልጠናውን ከተከታተሉ መካከል ወጣት ገሰሰው ገብረመድህን “ባንኩ የሰጠን በእውቀት ላይ የተመሰረተ ፕሮጀክት እንድንቀርፅና ሰርተን እንድንለወጥ መንገድ የሚያሳይ ነው “ ብሏል።
በተያዘው 2016 በጀት ዓመትም የወረቀትና የፕላስቲክ ማምረቻ ፋብሪካ ከፍቶ በግሉ ለመስራት የስራ እቅድ አዘጋጅቶ ለልማት ባንክ አቅርቦ መልስ እየተጠባበቀ መሆኑን ገልፅዋል።