ቀጥታ፡

የመደመር ዕሳቤ አገር በቀል እውቀቶችን ለችግሮቻችን መፍትሄ አድርገን እንድንጠቀም ዕድል የሰጠ ነው - ዶ/ር ሮባ ጴጥሮስ

አዲስ አበባ ፤ሃምሌ 27 / 2015 (ኢዜአ):-የመደመር ዕሳቤ አገር በቀል እውቀቶችን ለችግሮቻችን መፍትሄ አድርገን እንድንጠቀም ዕድል የሰጠ ነው ሲሉ የህግ ምሁሩ ዶክተር ሮባ ጴጥሮስ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ”መደመር ለህብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ አካሂዷል።


 

በውይይት መድረኩ ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶን ጨምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትር አዲሱ አረጋና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

በመድረኩም የመደመር እሳቤ ከአገር በቀል እውቀቶች ጋር ያለው ትስስር፤ ለተቋማት ግንባታ ያለው ሚና፤ መደመርና ሜጋ ፕሮጀክቶች እንዲሁም የመደመር ቀጣይ እድሎችና ፈተናዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ቀርቧል፡፡

የህግ ምሁር የሆኑት ዶክተር ሮባ ጴጥሮስ መደመርና ሀገር በቀል እውቀቶች በሚል ርዕስ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ጽሁፍ ኢትዮጵያ በህዝቦች መካከል አብሮነትና ሰላምን የሚያሰርጹ በርካታ የአገር በቀል እውቀቶች ባለቤት መሆኗን ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ "መደመር" የኢትዮጵያዊያን የልቦና ውቅር የሆኑ አገር በቀል እሴቶችን መሰረት ያደረገ እሳቤ መሆኑን ገልጸዋል።


 

እነዚህ አገር በቀል እሴቶች ደግሞ በአብሮነት የተሸመነ የጋራ ማንነት ላላቸው ኢትዮጵያውያን ከችግር መውጫ ቁልፍ መሳሪያዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በመሆኑም መደመር አገር በቀል እውቀቶችን ለችግሮቻችን መፍትሄ አድርገን እንድንጠቀም ዕድል የሰጠ ዕሳቤ መሆኑን ገልጸዋል። 

የመደመር ዕሳቤ የተውሶ ርዕዮተ ዓለምና አስተሳሰብ ውጤት የሆኑ ስብራቶችን ለማከም የሚያግዝ ነው ብለዋል።

የመደመር እሳቤ በተለይ ለመጻኢ የኢትዮጵያ ጉዞ ቀልፍ መሰረት የሆኑ ሰላምና አብሮነት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያውያን በትልቅነታችን ልክ እንዳንራመድ ከሚጎትቱን ጉዳዮች መላቀቅና በመደመር እሳቤ ህብረብሄራዊ አንድነትን ማጠንከር ይገባናል ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም