ኢትዮጵያ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ አድማሷን ለማስፋት እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ አድማሷን ለማስፋት እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 27/2015 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አድማሷን ለማስፋት ከተለያዩ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን የግንኙነት መስክ እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለፁ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ወቅታዊ የአገሪቱን የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በሰጡት መግለጫ፤ በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል በፕሪቶሪያው የተደረሰው የሰላም ስምምነትን ተከትሎ የአገሪቱ የውጭ ግንኙነት እንቅስቃሴ እየተሻሻለ መጥቷል።
ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን የግንኙነት መስክ እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸው፤ ወዳጅ የማጽናትና የማጠናከር ሥራው በአግባቡ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በአዲስ መልኩ የተጀመረው የዲፕሎማሲ ግንኙነት በተለይም በድኅረ-ጦርነት ዘላቂ የሰላም ግንባታ፣ የመልሶ ማቋቋምና የኢኮኖሚ ትብብር ላይ ትኩረት አድርጎ መንቀሳቀሱንም ነው ያነሱት።
እነዚህ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የተመራ መሆኑን አንስተው ለአብነትም በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከልዑካኖቻቸው ጋር በጣሊያንና በሩስያ ያደረጉትን ጉብኝት ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንትን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የበርካታ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ተወካዮች በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸውን ገልጸው፤ ይህም የአገሪቱ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን ሌላው ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።
የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ አድማሱን ለማስፋት በተሰራው ሥራ በርካታ አገራት ማቅረብና ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር ያስቻለና ግንኙነታቸውን በአዎንታዊ መልኩ የቀየረ መሆኑንም ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ በተለይም በሱዳንና ሶማሊያ ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ምጣኔ ኃብታዊ ትስስርን ለማሳለጥ እያደረገች ያለውን አዎንታዊ አስተዋጽዖ አጠናክራ መቀጠሏንም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የአባይን ውሃ በተመለከተ በፍትሃዊነትና በእኩልነት መጠቀም የሚለውን መርህ ማጠናከር የሚያስችል የተፋሰሱ አገራት የተሳተፉበት የተሳካ ስብሰባ በአዲስ አበባ መካሄዱን ገልፀዋል።