በበጀት ዓመቱ ከመዲናዋ ነዋሪዎች ለህዳሴ ግድብ ግንባታ 460 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ  ታቅዷል-የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ  ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2015 (ኢዜአ)፦በ2016 በጀት ዓመት ከመዲናዋ ነዋሪዎች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 460 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን በአዲስ አበባ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

በአዲስ አበባ በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት ለግድቡ ግንባታ በገቢ አሰባሰብ የላቀ ተሳትፎ ለነበራቸው ባለድርሻ አካላት የእውቅና መርሐ ግብር ተካሂዷል።

በአዲስ አበባ የታላቁ  የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ምሥክር ነጋሽ እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ለግድቡ ግንባታ ከ682 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል።

በ11ዱም ክፍለ ከተሞች ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የኅብረተሰብ ክፍሎች የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ ለዚህም ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

ገንዘቡ የተሰበሰበው በቦንድ ግዢና በስጦታ መሆኑን ገልጸው፤ የተሰበሰበው ገንዘብ በበጀት ዓመቱ በእቅድ ከተያዘው ገንዘብ ጋር ሲነጻጸር 99 ነጥብ 6 በመቶ አፈጻጸም እንዳለው ነው ያመላከቱት።

በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመትም  የመዲናዋን ነዋሪዎች በማስተባበር ለህዳሴ ግድብ ግንባታ 460 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን አቶ ምሥክር ጠቁመዋል።

የቦሌ ክፍለ ከተማ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ጌትነት ተዋበ፤ በክፍለ ከተማው ነዋሪውንና ባለሀብቱን በማሳተፍ የተሻለ የገንዘብ ድጋፍ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

በ2016 በጀት ዓመትም በተለያዩ የድጋፍ ማሰባሰቢያ መድረኮች ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ  እንደታቀደም ነው ያመላከቱት።

የአቃቂ ክፍለ ከተማ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሻምበል ሥዩም መኮንን በበኩላቸው በ2015 በጀት ዓመት ከክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን  ገልጸው፤ በ2016 በጀት ዓመት ዕቅዱን ለማሳካት ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል። 

ባለፉት 12 ዓመታት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችና ባለኃብቶችን ለህዳሴው ግድብ ግንባታ  ከ4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ደጋፍ ማድረጋቸው ተገልጿል።

ከ10 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችም በድጋፍ ማስባሰብ ሂደቱ በልዩ ልዩ መልኩ መሳተፋቸው ነው የተነገረው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም