የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን የተፈጥሮ ፀጋ በመጠቀም ወጣቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ ይመቻቻል-ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን የተፈጥሮ ፀጋ በመጠቀም ወጣቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ ይመቻቻል-ቢሮው
ሚዛን አማን ፤ሐምሌ 27/2015 (ኢዜአ) ፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ያለውን የተፈጥሮ ፀጋ በመጠቀም ወጣቶችን አደራጅቶ ወደ ሥራ እንዲገቡ የማመቻቸት ተግባር እንደሚከናወን የክልሉ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው በ2016 በጀት ዓመት የስራ ፈላጊ ወጣቶች ልየታና በዋናዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚመክር የንቅናቄ መድረክ በሚዛን አማን ከተማ እያካሄደ ነው።
የቢሮው ሀላፊ አቶ ግዛው ጋግያብ እንዳመለከቱት፤ የክልሉ መንግስት ሥራ ፈላጊ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት ሰፊ ሀብት በማመቻቸት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።
ባለፈው የበጀት ዓመት በገጠርና በከተማ በተለያዩ የስራ መስኮች ለ170 ሺህ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን አስታውሰዋል።
በዚሁ ወቅት በክልሉ በሚገኙ መዋቅሮች ለስራ ዕድል ፈጠራ ሥራ በቂ ሀብት ያለማመቻቸት፣ ከዚህ ቀደም የተሰራጨ የብድር ገንዘብን አለማስመለስ፣ የአካታችነት ችግር እንዲሁም የመስሪያና የመሸጫ ቦታ እጥረት እንደነበረ አውስተዋል።
የነበሩት ክፍተቶች በማስተካከል በተያዘው የበጀት ዓመት በክልሉ ያሉትን እምቅ የተፈጥሮ ፀጋዎች በተገቢው ተጠቅሞ ሥራ ፈላጊ ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት የማመቻቸት ተግባር እንደሚከናወን ገልጸዋል።
የክልሉ የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ተዘራ ወልደማሪያም በበኩላቸው ፤ የሥራ ዕድል ማመቻቸት ተግባር ከአድሎ በፀዳ መልኩ ማከናወን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በክልሉ የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶችን በተገቢው ለይቶና ሀብት መድቦ ወደ ስራ ማስገባት ያስፈልጋል ብለዋል።
በሀገር ደረጃ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ከሚለዩ ወጣቶች መካከል 50 በመቶው ሴቶች እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራ ከሰብአዊነት ጋር በቀጥታ የተገናኘ ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም መዋቅሮች ከተለመደው አካሄድ ወጥተው በመፍጠርና በመፍጠን ርብርብ እንዲያደርጉም አቶ ተዘራ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመድረኩም የክልሉ ምክር ቤትን ጨምሮ ከሁሉም ዞኖች የተውጣጡ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።