ቀጥታ፡

የመደመር እሳቤ ከሃይል ይልቅ በሃሳብ የበላይነት የሚመራ የፖለቲካ ባህል እንዲጎለብት መሰረት የጣለ ነው - አቶ ዛዲግ አብርሃ    

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 27/2015 (ኢዜአ):- የመደመር እሳቤ ከሃይል ይልቅ በሃሳብ የበላይነት የሚመራ የፖለቲካ ባህል እንዲጎለብት መሰረት የጣለ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካና ርዕዮተ-ዓለም ዘርፍ ሃላፊ  ዛዲግ አብርሃ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት “መደመር ለህብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ አካሂዷል። 

"ፈተናዎችና ቀጣይ ተስፋዎች" በሚል ርዕሰ ጉዳይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት አቶ ዛዲግ አብርሃ መደመር ኢትዮጵያን ሃሳብ ባጠራት ጊዜ የመጣ ትልቅ እሳቤ ነው ብለዋል።  

የመደመር እሳቤ የሰው ልጆች በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማኅበራዊ ዘርፎች ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያደርጉ አስተሳሰቦችን በውስጡ የያዘ ጥልቅ እሳቤ መሆኑንም ጠቁመዋል።  

መደመር ለአገር በቀል እውቀቶች ቅድሚያ የሚሰጥ ነው ያሉት አቶ ዛዲግ በተጨባጭ ለውጥ በማምጣት ላይ የሚገኝ ስለመሆኑም ተናግረዋል። 

የመደመር እሳቤ ኢትዮጵያ ባሏት ጸጋዎቿ ተጠቅማ እንድትበለጽግ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመው ሌሎችን መሆን ሳይሆን ራስን ሆኖ ማደግና መበልጸግ እንደሚቻል የሚያመላክት መሆኑን ገልጸዋል።


 

መደመር ከዚህ ቀደም ያልተኬደባቸውን መንገዶች የመረጠ መሆኑን ያነሱት አቶ ዛዲግ አገር በቀል እውቀቶች ከፍ እንዲሉና ለዕድገት መሰረት እንዲሆኑ ቅድሚያ የሚሰጥ ነው ብለዋል።  

"መደመር የማያቋርጥ ዕድገት ያለው እሳቤ ነው" ያሉት አቶ ዛዲግ አዲስ ሃሳብ፣ አዲስ መንገድና አዲስ ባህል እና ትውልድን የያዘ ነውም ብለዋል።  

የሃሳብ ግልጽነት፣ ብሔራዊ መግባባት፣ አገራዊ ምክክር፣ ለድርድርና ሰላም ዕድል መፍጠርና አረንጓዴ አሻራ የመደመር እሳቤ ተስፋዎች ናቸው ሲሉም ገልጸዋል። 

ለአዲስ የፖለቲካ ባህል መሰረት መጣል ና ሃሳብ ዋጋ እንዲያገኝ ማድረግም ሌላኛው የመደመር ተስፋዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም