የመደመር እሳቤ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ በሆነ መልኩ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማትና ሰላም የሚያረጋግጡ ተቋማት እንዲገነቡ አስችሏል--አቶ ሲሳይ ቶላ - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር እሳቤ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ በሆነ መልኩ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማትና ሰላም የሚያረጋግጡ ተቋማት እንዲገነቡ አስችሏል--አቶ ሲሳይ ቶላ
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 27/2015 (ኢዜአ):- የመደመር እሳቤ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ በሆነ መልኩ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማትና ሰላም የሚያረጋግጡ ተቋማት እንዲገነቡ አስችሏል ሲሉ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ ተናገሩ፡፡
በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አዘጋጅነት “መደመር ለህብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ ውይይት እየተካሄደ ነው።
በመድረኩም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ መደመርና የተቋማት ግንባታ በሚል ርእስ የውይይት መነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡
በዚህም አገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት ቅድሚያ ሰጥቶ ከሰራባቸው ጉዳዮች ዋነኛው የተቋም ግንባታ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ለውጥ በሚያስተናግድ አገር ውስጥ አዳዲስ ፍላጎቶች መምጣታቸው አይቀሬ ነው ያሉት አቶ ሲሳይ ቶላ፤ በኢትዮጵያም አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በርካታ ፍላጎቶች መቅረባቸውን አስታውሰዋል፡፡
ህግን መሰረት ባደረገ መልኩ ከተለያየ አቅጣጫ ለሚመጡ ፍላጎቶች ምላሽ ለመስጠት ደግሞ በቅድሚያ ጠንካራ ተቋማት እንደሚያስፈልጉ ነው የገለጹት፡፡
በመሆኑም መንግስት በመደመር እሳቤ ማዕቀፍ ውስጥ ሙያን መሰረት አድርገው የሚሰሩ ተቋማትን መገንባት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን ጠቅሰዋል።
በዚህ ረገድ በጸጥታና ደህንነት ተቋማት የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎችን ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
እነዚህ ተቋማት ባለፉት አምስት ዓመታት የገጠሙ ፈተናዎችን በመቋቋም የኢትዮጵያ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ በሆነ መልኩና ሙያን መሰረት በማድረግ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውንም ነው ያብራሩት፡፡
የመደመር እሳቤ ተቋማቱ ጽዱና ምቹ የስራ ከባቢን በመፍጠር ህዝብን እንዲያገልግሉ በማድረግ በኩልም አዲስ እይታ ማስተዋወቁን ጠቁመዋል፡፡