ኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ አንድነቷን በማጠናከር ፈተናዎችን ተቋቁማ በተጨባጭ የሚታዩና ተስፋ ሰጪ ድሎችን እያስመዘገበች ነው - ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ አንድነቷን በማጠናከር ፈተናዎችን ተቋቁማ በተጨባጭ የሚታዩና ተስፋ ሰጪ ድሎችን እያስመዘገበች ነው - ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 27/2015 (ኢዜአ) :- ኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ አንድነቷን በማጠናከር ፈተናዎችን ተቋቁማ በተጨባጭ የሚታዩና ተስፋ ሰጪ ድሎችን እያስመዘገበች መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አዘጋጅነት “መደመር ለህብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ ውይይት እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አገራዊ መግባባትን ሊፈጥሩ በሚችሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በተለያዩ ጊዜያት ለሚያደርገው ውይይት እውቅና ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡
አገራዊ ለውጡ እውን ከሆነ ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥና ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሀገር በቀል የሆነውን የመደመር እሳቤም ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር፣ ሰላምን ማስፈን እና የተለያዩ አካላት በአንድነት ለአገር ብልጽግና እንዲሰሩ ለማስቻል በማሰብ በመተግበር ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎች ቢያጋጥሟትም የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የልማት ጉዞ ላይ መሆኗን አንስተዋል።
በሀገሪቱ የፖለቲካ ስርዓት በራስ አቅምና በራስ ዕይታ መጓዝን የሚጠይቅ አዲስ ባህል መምጣቱን ገልጸው፤ በዚህ ሂደት ያጋጠሙ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ለብልፅግና መሳካት በርብርብ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታትም ኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ አንድነቷን በማጠናከር ያጋጠሟትን ፈተናዎች ተቋቁማ በተጨባጭ የሚታዩ እና ተስፋ ሰጪ ድሎችን እያስመዘገበች መሆኗንም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ስርዓት እድገት እያስመዘገበች ነው ያሉት ምክትል አፈ ጉባኤዋ፤ ከራሷ አልፋ ለሌሎች መትረፍ እንደምትችልም በጎረቤት አገራት ጭምር እያስፋፋች የምትገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ትልቁ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም ለውጡን ለማፅናት፣ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እንዲሁም የተገኙ እድሎችን ወደ ድል በመቀየር በኩል ማህበረሰቡን ለማስገንዘብ በስፋት እየሰራ መሆኑን አድንቀዋል።
በዛሬው “ መደመር ለህብረ ብሔራዊ አንድነት ”በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ ውይይትም የዜና አገልግሎቱ ለጀመራቸው ተግባራት ተጨባጭ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፤ ኢዜአ ከሚያቀርባቸው ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎች ባሻገር ብሔራዊ መግባባትን የሚፈጥሩና ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቁ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
ኢዜአ የተለያዩ ሀገራዊ የምክክር መድረኮችን ሲያካሂድ መቆየቱን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ኢትዮጵያውያን በቁልፍ ሀገራዊ ጉዳዮች ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጥሩ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ኢዜአ ከይዘት አኳያ ውጤት የሚያመጡ ተግባራትን እያከናወነ ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ይዘትን ከማበልጸግ ጎን ለጎን የሃሳብ ብዝሃነትን የማረጋገጥ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
ተቋሙ ለሰላምና ልማት የሚበጁ ሀሳቦችን የሚያመነጩ የዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን እና የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት በኩል፤ ከምንጊዜውም በላይ በሙሉ አቅሙ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ምክትል አፈ-ጉባኤዋን ጨምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።