ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተመናመኑ ብዝሃ ህይወት ከመመለስ ባለፈ ለዓለም ምሳሌ የሚሆን ተግባር ነው - የፕላንና ልማት ሚኒስቴር

 ሉሜ  ፤ ሐምሌ 27/2015 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተመናመኑ ብዝሃ ህይወት ከመመለስ ባለፈ የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል አንፃር ለዓለም ምሳሌ የሚሆን ተግባር መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር  ገለፀ።

የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣንን ጨምሮ ለፕላንና ልማት ሚኒስቴር ተጠሪ የሆኑ አራት የፌደራል ተቋማት በምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ ዶጎ ጉዴዶ ቀበሌ ከ23ሺህ በላይ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጡ ችግኞችን ተክለዋል።

የፕላንና ልማት  ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጥሩማር አባተ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት ሀገሪቷ የተያያዘችውን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት ዕቅድ እውን ማድረግ የምንችለው በአካባቢ ላይ በምንሰራው የደን ልማት ስራ ነው ብለዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው የዛሬውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩን በዋናነት እያስተባበረ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታዋ ዛሬ በምስራቅ ሸዋ ዞን ተገኝተን የተከልነው ችግኝ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ማሳኪያ አንዱ አካል ነው ብለዋል።

በተለይም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ሊመጡ የሚችሉ ተፅዕኖዎችን መቋቋም የሚችል የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ በቀጣይ አስር ዓመታት እውን ለማድረግ በአረንጓዴ አሻራው ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን  ውጤታማነቱንም ክትትል እያደረግን ነው ብለዋል።

"በተለይም የካርበን ልቀትን በመቀነስ ረገድ ለዓለም ምሳሌ የሚሆን ስራ እየሰራን ነው" ያሉት ወይዘሮ ጥሩማር፤ አሁንም ስራውን በማስተባበርና በመምራት ረገድ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በክረምት በጎ ፍቃድ ስራ ባለፈው ዓመት አፋር ክልል ካሳ ጊታ ወረዳ የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳትና የተማሪዎች መማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው፤ በዘንድሮው የክረምት በጎ ፍቃድ ስራ ደግሞ በሉሜ ወረዳ ተመሳሳይ ስራዎችን ለማከናወን የልየታ ስራ መስራታቸውን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታሁን ጋረደው በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ማሳካት ለአካባቢና ስነ ምህዳር ልማት ወሳኝ በመሆኑ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለመቋቋምም ብቸኛ አማራጭ መሆኑን ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም ኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ላይ በትኩረት ስትሰራ ሀገራችንን ጨምሮ ዓለም ለገጠመው የዘርፉ ፈተናዎች ፍቱን መድኃኒት ላይ እየሰራች መሆኑን ማረጋገጫ ነው ብለዋል።

ሀገራችን የዘንድሮውን ጨምሮ ባለፉት አምስት ዓመታት የተከለቻቸው ችግኞች ለተመናመነው ብዝሃ ህይወት የዘር ባንክ እንደመትከል ነው ያሉት ዶክተር ጌታሁን፤ የአየር ብክለትና ብክነትን ለማስተካከል ሚናው የላቀ መሆኑንም አመልክተዋል።

ከችግኝ ተከላው ጎን ለጎን የክረምት በጎ ፍቃድ ስራዎች በተለይም የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ፣ የተማሪዎችን የመማሪያ ቁሳቁስ ማሰባሰብና ደም መለገስ ላይ ትኩረት አድርገው እየሰሩ መሆኑን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታሁን ጋረደው ገልጸዋል።

በችግኝ ተከላው መርኃ-ግብር ላይ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል ወይዘሮ ተጓደላ እንዳወቅ በየዓመቱ የምንተክላቸውን ችግኞች ከመትከል ባለፈ ውሃ እያጠጣን እየተንከባከብን እንገኛለን ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም