ቀጥታ፡

የመደመር ጽንሰ ሃሳብ አንደኛው ያለ ሌላኛው ሕልውና እንደሌለው የሚያመላክት የህብረ ብሔራዊ አንድነት መሰረት ነው--አቶ አዲሱ አረጋ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 27/2015 (ኢዜአ) :- የመደመር ጽንሰ ሃሳብ አንደኛው ያለ ሌላኛው ሕልውና እንደሌለው የሚያመላክት የህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማስቀጠል መሰረት መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ ተናገሩ።

የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ባህል ለማዳበር የልዩነት ኃሳቦች የሚንሸራሸሩበት የውይይትና የምክክር መድረኮች ማስፋት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በኢዜአ አዘጋጅነት "መደመር ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ አገር አቀፍ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ባህል ለማዳበር የልዩነት ኃሳቦች የሚንሸራሸሩበት የውይይትና የምክክር መድረኮች ማስፋት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በዚሁ መነሻነትም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለዴሞክራሲ ባህል ማበብ ተቋማዊ ኃላፊነቱን በመወጣት የሃሳብ የበላይነት እንዲጎለብት እያደረገ ለሚገኘው ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።

የመደመር ጽንሰ ሃሳብም አገራዊ አውድን መሰረት በማድረግ ኢትዮጵያ ችግሮቿን የምትፈታበትን መፍትሄ አመላካች ሃሳቦችን የወለደ አገር በቀለ የሃሳብ ካዝና እንደሆነም ገልጸዋል።

የመደመር ፅንሰ ሃሳብ አገር በቀል እሳቤ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የታሪክ ጠባሳ የሆኑና የርዕዮተ ዓለም ግትርነት የወለዳቸውን እንቅፋቶች መፍትሔ መስጠት የሚያስችል እሳቤ ነው ብለዋል።

በመጠላለፍና በልዩነት ትርክት ላይ የተገነባው የፖለቲካ ባህል ኢትዮጵያን ዋጋ እያስከፈላት መሆኑን ጠቅሰው፤ የመደመር ጽንሰ ሃሳብም አብሮነትና መደጋገፍን በማጎልበት ህብረ ብሄራዊ አብሮነት ለማስቀጠል መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።


 

በኢትዮጵያ እየተስተዋለ የሚገኘው ዋልታ ረገጥ አስተሳሰብ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት መጎልበትና ለመደመር እሳቤ ሳንካ እየሆኑ መምጣታቸውንም አንስተዋል።

ጽንፍ የመያዝና "እኔ ያልኩት ካልሆነ" የሚል ግትርነት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ሆኖ መቆየቱን አንስተው፤ ይህ አይነቱ አካሄድ ለአገር ህልውና የማይበጅ በመሆኑ በመደመር መርህ መጓዝ ያስፈልጋል ብለዋል።

መደመር ለህብረ ብሄራዊ አንድነት ያለው ጠቀሜታ አንደኛው ያለ ሌላኛው ህልውና እንደሌለው እስከማሰብ ድረስ የሚዘልቅ የአብሮነት መሰረት ልክ መሆኑን ገልፀው የመደመር እሳቤ ሊጠናከር ይገባል ነው ያሉት።

እንዲህ አይነት ውይይቶችም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ነው አቶ አዲሱ የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም