ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር እያከናወናቸው ያላቸውን ተግባራት አጠናክሮ መቀጠል አለበት- ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 27/2015 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እያከናወናቸው ያለውን ተግባራት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ አሳሰቡ።

“መደመር ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የተዘጋጀው አገር አቀፍ ውይይት እየተካሄደ ነው።

“አገራዊ ለውጡ እውን ከሆነ ጊዜ ጀምሮ ማንኛውም የውጭ አካል ኢትዮጵያን በራሱ አተያይና እሳቤ ጫና ሊያደርግባት በማይችልበት ደረጃ ለዜጎች በሚጠቅም የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ብቻ ለመጓዝ ኢትዮጵያ የራሷን ጉዞ መከተል ጀምራለች” ሲሉ ወይዘሮ ሎሚ ገልጸዋል።

የራስን መንገድ አስጠብቆ የመጓዝ ሂደት ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዞ አዲስ ነው ያሉት ምክትል አፈ ጉባኤዋ ፈተናዎች ቢኖሩም ወደ ብልጽግና የሚያራምዱ አዳዲስ እይታዎችን መምጣታቸውን አመልክተዋል።

በዚህም በኢትየጵያ የሚተይ እና ተስፋ ሰጪ እድሎች እንዲመዘገቡ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።


 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሀሳብ አፍላቂነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ኢትዮጵያውያን ከራሳችን አልፈን ለሌሎች መትረፍ እንደምንችል ያሳየንበት ነው ብለዋል ምክትል አፈ-ጉባኤዋ።

የተገነቡ እና እየተገነቡ ያሉ አገራዊ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያውያን አገር በቀል እውቀታቸውን ተጠቅመው ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚችሉ የሚያሳይ መሆኑን አመልክተዋል።

ከዚህም አኳያ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አገራዊ ለውጡን ይዞ እየተጓዘ ባለው የመደመር እሳቤ ላይ ያሉ እድሎች፣ ፈተናዎች እና መውጫ መንገዶች ተገንዝቦ የውይይት መድረክ ማዘጋጀቱን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

ኢዜአ ከተሰጡት ተልዕኮዎች አንዱ በሆነው የብሔራዊ መግባባት የመፍጠር አጀንዳ ስራ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ምክትል አፈ-ጉባኤዋ አሳስበዋል።

በመድረኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም