ቀጥታ፡

የአፍሪካ ሀገራት ከኢትዮጵያ የተቋማት የአክሪዲቴሽን አገልግሎት ለማግኘትና በትብብር ለመስራት እየጠየቁ ነው--የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 27/2015 (ኢዜአ) :- የአፍሪካ ሀገራት ከኢትዮጵያ የተቋማት የአክሪዲቴሽን አገልግሎት ለማግኘትና በትብብር ለመስራት እየጠየቁ መሆኑን የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ገለጸ።

የኢትዮጵያን የአክሪዲቴሽን ወሰን በማስፋት የአገር ውስጥ ምርትና አገልግሎቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነታቸው እንዲጨምር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ገልጿል።

አገልግሎቱ በ2003 ዓ.ም የተቋቋመ የጥራት ድርጅት ሲሆን፤ በ2008 ዓ.ም በሕክምና እና በፍተሻ ላቦራቶሪ ዓለም አቀፍ ዕውቅና አግኝቷል።

በየአራት ዓመቱ በሚደረግለት ግምገማ የዕውቅና ወሰኑን በማስፋት በመስከረም ወር 2012 ዓ.ም ደግሞ በሰርተፊኬሽንና በኢንስፔክሽን ተጨማሪ እውቅና ማግኘት ችሏል፡፡

በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም ደግሞ በዓለም አቀፍ አክሪዲቴሽን መድረክ ላይ በሲስተም ሰርቲፊኬሽን የባለብዙ ወገን የእውቅና ስርዓት አባል ሆኖ ሰርተፊኬቱን አግኝቷል።

የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት በዓለም አቀፉ የላቦራቶሪ አክሪዲቴሽን ኮርፖሬሽን (ILAC) እና በዓለም አቀፍ አክሪዲቴሽን መድረክ (IAF) ተመዝኖ ብቃቱ የተረጋገጠ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር መሠረት ተሰማ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በመጪው መስከረም 2016 ዓ.ም በምርት እና በካሊብሬሽን ላቦራቶሪ አክሬዲቴሽን ዕውቅና ታገኛለች ተብሎ ይጠበቃል።

ይህም ከአገር ውስጥ ባሻገር ለጎረቤት ሀገራት የተስማሚነት ምዘና ተቋማት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም አገልግሎቱ ከዚህ ቀደም እውቅና ባገኘባቸው በሕክምና፣ በኢንስፔክሽን፣ በሰርቲፊኬሽን እና በሲስተም ሰርተፊኬሽን አገልግሎት አሰጣጡ ተግምግሞ እውቅናው እንዲቀጥል ተወስኗል ነው ያሉት።

ዕውቅና በተገኘበት በፍተሻ ላቦራቶሪ እና በምርት ሰርተፊኬሽን አምራቾች የዓለም አቀፍ መስፈርት ያሟላ ምርት ወደ ውጭ በመላክ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል።

የአክሪዲቴሽን ተቋም የሌላቸው የጎረቤት አገራት ከኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ጋር ለመሥራት ፍላጎት እያሳዩ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል።

ከሶማሊያ ጋር የመግባቢያ ሥምምነት ለመፈራረም በሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ዑጋንዳና ሴኔጋል ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ሆስፒታሎች በሦስተኛ ወገን የላቀ የብቃት ማረጋገጫ መስጠት የሚያስችል የቴክኒክ ኮሚቴ አዋቅሮ እየሰራ ነው ብለዋል።

ይህም የህክምና ቱሪዝሙን ከማሳደግ አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት በ2015 በጀት ዓመት ለ12 ተቋማት አዲስ የሶስተኛ ወገን የላቀ ብቃት ማረጋገጫ የአክሪዲቴሽን ምስክርነት መስጠቱን አስታወቋል።

አዲስ እውቅና የተሰጣቸው ሰባት የሕክምና ላቦራቶሪዎች፣ ሦስት የፍተሻ ላቦራቶሪዎች እንዲሁም አንድ የግል ላቦራቶሪ በካሊቢሬሽን መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ተስማሚነት ኢንተርፕራይዝ ደግሞ የአክሪዲቴሽን እውቅና የተሰጠው ብቸኛ የመንግስት ድርጅት ነው።

የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት የዓለም አቀፍ አስገዳጅ መስፈርት ማሟላት ያልቻሉ 10 የሕክምና ላቦራቶሪዎች፣ 14 የፍተሻ ላቦራቶሪዎች እና አራት በኢንስፔክሽን የተሰማሩ ተቋማት አገልግሎት መስጠት እንዲያቋርጡ መደረጉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም