ቀጥታ፡

በውጭ አገራት የሚገኙ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አደረጃጀቶች ለኢትዮጵያ ወቅታዊ ጥሪዎች እና ፕሮጀክቶች የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 27/2015 (ኢዜአ) :- መንግስት በውጭ አገራት የሚገኙ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አደረጃጀቶች ለኢትዮጵያ ወቅታዊ ጥሪዎች እና ፕሮጀክቶች የሚያደርጉትን ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥሉ ጥሪ አቀረበ።

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የተውጣጣ የልዑካን ቡድን በሳዑዲ አረቢያ ሪያድ የኮሚኒቲ አደረጃጀት አመራሮችና ተወካዮች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ከሚሲዮን መሪዎችና ከኤምባሲው ሰራተኞች ጋር ተወያይቷል።

በውይይቱ ወቅት በሪያድና አካባቢው የሚኖሩ የኮሚኒቲ አደረጃጀቶችና የዳያስፖራ አባላት ለአገራዊ ፕሮጀክቶችና ወቅታዊ አገራዊ ጥሪዎች እያደረጉ ላለው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርቧል።

ከድጋፉ ባሻገር በአገር ቤት በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ ተጠይቋል።


 

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በኢትዮጵያ ጉዳይ ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የልዑካን ቡድኑ በሪያድ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤትንና የኮሚኒቲ አደረጃጀት ቢሮዎችን የጎበኘ ሲሆን ከኃላፊዎቹ ጋር ውይይት ማድረጉን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም