ህብረት ስራ ማህበራት በሀገሪቱ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የሚጫወቱት ሚና ወሳኝ ነው - ኮሚሽነር ዶክተር ጌታቸው መለስ - ኢዜአ አማርኛ
ህብረት ስራ ማህበራት በሀገሪቱ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የሚጫወቱት ሚና ወሳኝ ነው - ኮሚሽነር ዶክተር ጌታቸው መለስ
ድሬደዋ ፤ ሀምሌ 26 /2015(ኢዜአ)፡- የህብረት ስራ ማህበራት የምርትና አገልግሎት ተደራሽነትን በማሳደግ በሀገሪቱ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የሚጫወቱት ሚና ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ጌታቸው መለስ ገለጹ።
"የህብረት ስራ ማሀበራት አጋርነት ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሀሳብ አለምአቀፍ የህብረት ስራ ማህበራት ቀን በድሬዳዋ እየተከበረ ነው።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ጌታቸው መለስ ባደረጉት ንግግር፤ የህብረት ስራ ማህበራት በሀገሪቱ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የሚጫወቱት ሚና ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ሚናቸው የምርትና አገልግሎት ተደራሽነትን በማሳደግ ፣ በድህነት ቅነሳና በስራ ፈጠራ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዘርፉን ክፍተቶች በማስተካከልና መሠረታዊ ሪፎርም በማካሄድ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ በበኩላቸው፤ ግብርናን ከኢንዱስትሪ ጋር በማስተሳሰር የተደራጁ አርሶና አርብቶ አደሮች ምርት እሴት በመጨመር ለኢንዱስትሪው ሽግግር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በማህበራዊ ና በምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች በርካታ ተግባራት እያከናወኑ ናቸው ብለዋል።
ተደራሽነታቸው በጥራትና በመጠን የበለጠ ከማሳደግና አምራቹን ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር የአደረጃጀት ፣ የአሰራር፣ የፋይናንስ አቅርቦትና የመሠረተ ልማት አለመሟላት ለማስተካከል ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለፃ ፤ የህብረት ስራ ማህበራት የተጀመረውን ሀገራዊ የብልፅግና ጉዞ ከዳር በማድረስ ሂደት ውስጥ የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው።
የህብረት ስራ ማህበራት የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን የተናገሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ናቸው።
ይበልጥኑ የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል እያበረከቱት የሚገኙት አስተዋጽኦ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።
በድሬደዋ አስተዳደር ገጠርና ከተማ በተለያዩ ዘርፎች የተደራጁ ከ97ሺህ በላይ አባላትና ከ126 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያላቸው ከ1ሺህ 100 በላይ መሠረታዊ ማህበራትና ሶስት ዩኒየኖች እንደሚገኙ አስረድተዋል።
የአስተዳደሩን ማህበራዊና ምጣኔ ሃብት በማሳደግና ፍትሃዊ የገበያ ስርአት እንዲሰፍን እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።
የድሬዳዋ የግብርና ፣ውሃ ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ እንዳሉት፤ በአስተዳደሩ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራት የግብርና ምርታማነት እንዲጨምር ብሎም የዜጎችን የኑሮ ውድነት በማቃለል ረገድ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
በድሬዳዋ እየተከበረ ባለው አለምአቀፍ የህብረት ስራ ማህበራት ቀን ላይ የሚገኙ መልካም ተሞክሮዎች የተሻለ መስራት እንደሚያግዙ ገልጸዋል።
ዛሬ በተጀመረውና እስከ ነገ በሚቀጥለው የህብረት ስራ ማህበራት ቀን ላይ ከፌደራልና ከክልሎች የተወጣጡ የዘርፉ አመራሮች እየተሳተፉ ሲሆን በዘርፉ የተከናወኑ ምርጥ ተሞክሮዎች ዙሪያ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።