በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በተገነቡ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ከ48 ሺህ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሆነዋል- መምሪያው - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በተገነቡ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ከ48 ሺህ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሆነዋል- መምሪያው
ጎንደር፤ ሐምሌ 26/2015 (ኢዜአ):- በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ54 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በተገነቡ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ከ48 ሺህ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን የዞኑ ውሃና ኢነርጂ መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ይመር ለኢዜአ እንደገለጹት በ2015 በጀት ዓመት በዞኑ ለንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ተደራሽነት ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል፡፡
በዞኑ ስር በሚገኙ 15 ወረዳዎች 239 የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልገሎት መብቃታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ከ48 ሺህ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ከውሃ ፕሮጀክቶቹ 183 የእጅ ጉድጓዶች፣19 የጎለበቱ ምንጮች ፣30 መለስተኛ ጥልቅ ጉድጓዶችና ሰባት በገመድ ስበት የሚሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ የዋለው ገንዘብ ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተገኘ መሆኑን ጠቁመው ሕብረተሰቡ በጥሬ ገንዘብ፣ በጉልበትና በቁሳቁስ ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ነው አቶ ብርሃኑ የገለጹት።
በፕሮጀክቶቹ ቀደም ሲል 56 በመቶ የነበረው የዞኑ የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ወደ 57 በመቶ ከፍ ማለቱን አመልክተዋል።
ፕሮጀክቶቹ በገጠሩ አካባቢ የሚኖረውን ሕዝብ ጤንነቱ ተጠብቆ አምራች ኃይል እንዲሆን በማድረግ ጠቀሜታቸው የጎላ ነው ብለዋል።
በበጀት አመቱ ከአዲስ ግንባታዎች በተጨማሪ በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ደርሶባቸው አገልግሎት መስጠት ያቋረጡ 295 የውሃ ፕሮጀክቶች ተጠግነው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ነው የመምሪያው ኃላፊ የገለጹት።
ለሕብረተሰቡ የሚሰራጨው የመጠጥ ውሃን ጥራቱና ደህንነቱ የተጠበቀ ለማድረግ በ9 ሺህ 442 የውሃ ተቋማት ላይ የውሃ ጥራት ፍተሻ በማካሄድ በኬሚካል የማከም ስራ መከናወኑን አክለዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው ፕሮጀክቶቹ የዞኑ ነዋሪዎች ውሃ ለመቅዳት የሚያደርጉትን አድካሚ ጎዞ በማስቀረት የውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።
ፕሮጀክቶቹ ጉልበታቸውን ከመቆጠብ በተጨማሪ ይገጥማቸው የነበረውን ጤና እክል ማቃለሉን አመልክተዋል።