ሕዝቡ በአገራዊ ምክክሩ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን የማኅበረሰብ መገናኛ ብዙኃን ግንዛቤ በማስጨበጥ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ሕዝቡ በአገራዊ ምክክሩ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን የማኅበረሰብ መገናኛ ብዙኃን ግንዛቤ በማስጨበጥ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተጠየቀ
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 26/2015 (ኢዜአ) ፡- ሕዝቡ በአገራዊ ምክክሩ በንቃት እንዲሳተፍ የማኅበረሰብ መገናኛ ብዙኃን ግንዛቤ በማስጨበጥ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው ተጠየቀ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን "በአካታች ብሔራዊ ምክክር ላይ የማኅበረሰብ መገናኛ ብዙኃን ሚና" በሚል መሪ ኃሳብ ለማኅበረሰብ መገናኛ ብዙኃን አመራሮችና ባለሙያዎች በቢሾፍቱ ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል።
በሥልጠናው ማስጀመሪያ ላይ የተገኙት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መሃመድ እድሪስ የማኅበረሰብ መገናኛ ብዙኃን አገርን በመገንባት በኩል ከፍተኛ ሚና ያላቸው በመሆኑ በእውቀትና በቁሳቁስ ሊታገዙ ይገባል ብለዋል።
ሥልጠናው መገናኛ ብዙኃኑ አገራዊ ምክክሩን አስመልክተው በእውቀት ላይ የተመሰረተ መረጃዎችን ለሕዝቡ ተዳራሽ እንዲያደርጉ ያግዛቸዋል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አባል ኮሚሽነር ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ በበኩላቸው ኮሚሽኑ የሚያከናውናቸው ተግባራት ህዝቡ ጋር ተደራሽ እንዲሆኑ የማኅበረሰብ መገናኛ ብዙሃኃን ትልቅ ሚና አላቸው ብለዋል።
መገናኛ ብዙኃኑ ኮሚሽኑ እስከ አሁን ያከናወናቸውን ተግባራት ሕዝቡ ጋር እንዲደርስ የሰሩትን ሥራዎች ለውደፊትም አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
በመድረኩ ሕዝቡ በአገራዊ ምክክሩ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆንና የምክክር ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን የማኅበረሰብ የመገናኛ ብዙኃን ግንዛቤ በማስጨበጥ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተጠይቋል።
ሥልጠናውም ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚቀጥል ሲሆን በተለያዩ ክልሎች ከሚገኙ የማኅበረሰብ መገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ከስልጠናው ጎን ለጎን ለ34 የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።