ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር በአረንጓዴ ልማት በጋራ የመስራት ፍላጎት እንዳላት ገለጸች - ኢዜአ አማርኛ
ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር በአረንጓዴ ልማት በጋራ የመስራት ፍላጎት እንዳላት ገለጸች
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 26/2015(ኢዜአ)፡- ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር በአረንጓዴ ልማት መስክ በትብብር መስራት እንደምትፈልግ አስታወቀች።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በኢስላማባድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ተከናውኗል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር፣ የፓኪስታን አቪዬሽንና የምድር ባቡር ሚኒስትር ካዋጃ ሰዓድ ራትፊክ፣ የፓኪስታን አደንዛዥ ዕጽ ቁጥጥር ሚኒስትር ናዋብዛዳ ቡግቲ፣ የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር የዘላቂ ልማት ግቦች አማካሪ ሮሚና ኩርሼድ አላም፣ ሌሎች የአገሪቷ ባለስልጣናት፣ አምባሳደሮች እና የፓኪስታን መገናኛ ብዙሃን ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል፣ ለዘላቂ ልማት፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ታሳቢ በማድረግ አረንጓዴ አሻራን ማስጀመራቸውን አምባሳደሩ ገልጸዋል።
መርሐ-ግብሩን ተከትሎ ኢትዮጵያ የተለያዩ የፍራፍሬ አይነቶችን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ላይ እንደምትገኝ አመላክተዋል።
አረንጓዴ አሻራ በምግብ ራስን ለመቻል፣ ድርቅን ለማስወገድ፣ ወቅቱን የጠበቀ ዝናብ ለማግኘት ብሎም ለውሃ ሀብት ልማት ስራ ወሳኝ አበርክቶ አለው ብለዋል።
በሌላ በኩል የፓኪስታን አቪዬሽንና የምድር ባቡር ሚኒስትር ካዋጃ ሰዓድ ራትፊክ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ወደ ፓኪስታን ተስፋፍቶ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለው መርሐ-ግብር ዓለም ላይ የተደቀነውን የአየር ንብረት ለውጥ ፈተና ለመፍታት እንደ አማራጭ መፍትሔ ሊወስዱት የሚችል መሆኑን አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር እያከናወኑት ላለው ተግባር ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የፓኪስታን አቪዬሽንና የምድር ባቡር ሚኒስትር ካዋጃ ሰዓድ ራትፊክ እና በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ያከናወነቻቸው ተግባራት እና የተገኙ ውጤቶችን የተመለከተ የጋራ መግለጫ ለፓኪስታን መገናኛ ብዙሃን መስጠታቸውን በኢስላማባድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።