ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን አባላት ዲሲ ዩናይትድ እግር ኳስ ክለብን ጎበኙ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 26/2015 (ኢዜአ) ፡- የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን አባላት በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘውንና በአሜሪካ ሜጀር ሊግ ሶከር የሚጫወተውን ዲሲ ዩናይትድ እግር ኳስ ክለብን ጎብኝተዋል።

በክለቡ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያዊው ባለሀብት ኢዮብ ማሞ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በቡድኑ እንዲጫወቱ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማካሄድ አሜሪካ መግባቱ ይታወሳል።

ብሔራዊ ቡድኑ በዲሲ ዩናይትድ ክለብ ባለድርሻ በሆኑት ኢትዮጵያዊው ባለሀብት ኢዮብ ማሞ አማካኝነት ክለቡ የሚጫወትበት ኦውዲ ፊልድ ስታዲየም መጎብኘታቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገልጿል።

ለቡድኑ ተጫዋቾች በስታዲየሙ በሚገኝ ሬስቶራንት ግብዣ እንደተደረገላቸው እና በአሜሪካ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጋር ቆይታ ማድረጋቸውን ገልጿል።

ኢዮብ ማሞ ብሔራዊ ቡድኑ ወደ አሜሪካ በመምጣቱ መደሰታቸውን ገልጸው በአሜሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ከጉያና ጋር በሚያደርገው ጨዋታ በስታዲየም ተገኝቶ ቡድኑን እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።

በክለቡ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች እንዲጫወቱ ያላቸውን ፍላጎት የገለጹት ባለሀብቱ የብሔራዊ ቡድኑ አባላትን ጨምሮ በስብስቡ ውስጥ ያልተካተቱ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች የሙከራ እድል አግኝተው መልማዮችንና የክለቡ አሰልጣኞችን ማሳመን ከቻሉ ክለቡን እንደሚቀላቀሉ ቃል ገብተዋል።

ብሔራዊ ቡድን በቨርጂኒያ ግዛት በሚገኘው ሴግራ ፊልድ ስታዲየም ዛሬ ከሌሊቱ 8 ሰአት ከጉያና ብሔራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታውን ያደርጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም