መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎችን መቀበል ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎችን መቀበል ጀመረ
መቀሌ ፤ ሐምሌ 26/2015 (ኢዜአ)፡- መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አቋርጠው የነበሩ ተመራቂ ተማሪዎችን ከትላንት ጀምሮ መቀበል መጀመሩን አስታወቀ።
የዩኒቨርሲቲው ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ትካቦ ገብረስላሴ ለኢዜአ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው አሁን ላይ በተፈጠረው ሰላም ለምረቃ አንድ ሴሚስተር ሲቀራቸው ትምህርታቸውን ያቋረጡ የቅድመና ድህረ ምረቃ ተማሪዎችን ለማስተማር መቀበል ጀምሯል።
ተመራቂ ተማሪዎቹ በጤና ሳይንስ፣ በቢዝነስና አስተዳደር፣ በህግ፣ በምህንድስና፣ በግብርና ሳይንስ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ጨምሮ በሌሎች የትምህርት ዓይነቶች የተከታተሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹን እየተቀበለ ምዝገባ መጀመሩንና ከኦሬንቴሽን በኋላ ወደ መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደት የሚገቡ መሆኑን አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹን ተቀብሎ ለማስተማር የሚያስችለውን የምግብ፣ የመኝታና ሌሎች አገልግሎቶች ዝግጅት ማድረጉን ዶክተር ትካቦ አስታውቀዋል።
በግቢው ሲመዘገቡ ከነበሩ ተመራቂ ተማሪዎች መካከል የሶሾሎጂ ተማሪ ዮሴፍ ብርሃነ መስቀል “የተረጋጋ ሰላም በመፈጠሩ አቋርጠነው የነበረውን ትምህርት ለመቀጠል በመብቃታችን ደስተኛ ነኝ” ብሏል።
“ትምህርት በመቋረጡ ወደ ቤተሰቦቼ ሄጄ ቆይቻለሁ፤ አሁን ግን በዩኒቨርሲቲው በቀረበው ጥሪ መሰረት ያቋረጥኩትን ትምህርት ለመጨረስና ለምረቃ ለመብቃት በመዘጋጀቴ ደስተኛ ነኝ” ያለችው ደግሞ በህክምና ሳይንስ የነርሲንግ ተማሪ ሰላም ጎይተኦም ናት።