ቀጥታ፡

በተፋሰስ አካባቢዎች የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ሊፈጠር ከሚችል ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊጠነቀቁ ይገባል - የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 26/2015 (ኢዜአ) ፦ በነሐሴ ወር በኢትዮጵያ ተፋሰሶች ላይ የሚኖረውን ከፍተኛ የዝናብ ስርጭት ተከትሎ ሊፈጠር ከሚችል ቅጽበታዊ ጎርፍ መጠንቀቅ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ።

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በመጪው ነሐሴ ወር በሰሜን ምስራቅ የአገሪቱ ስፍራዎች ካለፈው ወር አኳያ በዝናብ ስርጭቱ ላይ በአንጻራዊነት የመዳከም አዝማሚያ ሊኖር እንደሚችል ጠቁሟል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በተጠቀሱት ስፍራዎች የሚገኘው የእርጥበት መጠን የመቀነስ አዝማሚያ እንደሚኖረውና ይህም ለአካባቢው የግብርና እንቅስቃሴ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው አመልክቷል።

ያም ሆኖ በአካባቢው የሚገኘውን አነስተኛ እርጥበት አርሶ አደሩ በተገቢው መንገድ ሊጠቀምበት እንደሚገባ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።

በሰሜን ምስራቅ፣ በሰሜን፣ በመካከለኛው፣ በደቡብ ምዕራብና በምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች ከሚጠናከሩ የደመና ክምችቶች የተነሳ ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው እርጥበት ሊኖር እንደሚችል በመግለጫው ተገልጿል።

ይህም ለእጽዋት ልምላሜና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሻሻል አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ኢንስቲትዩቱ ያመለከተው።

ይህም ሁኔታ የአፈር ውስጥ እርጥበትን ከማሻሻል አንጻር አስቀድመው የተዘሩና በተለያዩ የእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ የመኸር ሰብሎች እንዲሁም ለተለያዩ የቋሚ ተክሎችና የጓሮ አትክልቶች የውሃ ፍላጎት ከማሟላት አንጻር ጠቀሜታ ይኖራዋል ተብሏል።

በሌላ በኩል በነሐሴ ወር የክረምት እርጥበት ተጠቃሚ በሆኑ የአገሪቱ ተፋሰሶች ላይ የዝናብ ስርጭት ከፍተኛ እንደሚሆን ነው የትንበያ መረጃው የሚያሳየው።

በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በደቡብ ምዕራብ፣ በመካከለኛው እንዲሁም በሰሜን ምስራቅ የአገሪቱ ተፋሰሶች የዝናብ ሁኔታው እየተጠናከረ እንደሚሄድም ተመላክቷል።

በአብዛኛው አባይ፣ ተከዜ፣ አዋሽ፣ ባሮ አኮቦ፣ ኦሞ ጊቤ፣ አፋር ደናክል፣ የላይኛውና የመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ፣ የላይኛው ዋቢ ሸበሌና ገናሌ ዳዋ ተፋሰሶች ላይ የተሻለ እርጥበት እንደሚኖርም ተጠቁሟል።

ይህም ለውኃ ኃብት መጨመር አወንታዊ ጎን እንደሚኖረው ነው የትንበያ መረጃው የሚያመለክተው።

ሊኖር ከሚችለው ከፍተኛ ዝናብ ጋር ተያይዞ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ ተፋሰሶችና ንዑስ ተፋሰሶች ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተትና የወንዞች ሙላት ሊከሰት እንደሚችል ተጠቁሟል።

በዚህም የሚመለከታቸው አካላት እንዲሁም ማህበረሰቡ በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም