ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ስራ እንዲጀምሩ የሚፈቅዱ የሕግ ማዕቀፎችን በማጠናቀቅ ላይ ነው- የባንኩ ገዥ ማሞ ምህረቱ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 26/2015 (ኢዜአ) :-  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ገብተው ስራ እንዲጀምሩ የሚፈቅዱ የሕግ ማዕቀፎችን በማጠናቀቅ ላይ  እንደሚገኝ የባንኩ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።

የባንኩ ገዥ ባንኩ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለማሳካት የሶስት ዓመት መርሐ-ግብር ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለማረጋገጥም የፊስካል ፖሊሲ አተገባበርን ውጤታማ ማድረግ፣ ጥብቅ የገንዘብ ቁጥጥርን ማጠናከር እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ መረጋጋትን መፍጠር እንደ ግብ መያዛቸውን አመልክተዋል።

በዚህም የዋጋ መረጋጋትን ለማምጣት በትኩረት እንደሚሰራ ጠቅሰው የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎታቸውን እንዲያሻሽሉ፣ የዲጂታል አሰራራቸውን እንዲያፋጥኑና የፋይናንስ አካታችነትን እንዲያስፋፉ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ በጥቅል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለኢንቨስትመንት ምቹ ምህዳርን ለመፍጠር የተያዘውን ግብ ለማሳካት በፋይናንስ ዘርፉም ትኩረት መሰጠቱን ነው የባንኩ ገዥ ያነሱት።

በተለይም የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ክፍት ለማድረግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑንና የኢትዮጵያ ባንኮችም ለውድድር መዘጋጀት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ገብተው ስራ እንዲጀምሩ የሚፈቅዱ የሕግ ማዕቀፎችም በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውንም እንዲሁ።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በሁሉም የኢኮኖሚ እድገት ምንጮች ስኬት ለማስመዝገብና የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያን ወደ ተግባር ማስገባቷን ጠቅሰዋል።

በተለይም የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትርጉም ያለው እድገት በሚያስመዘግብ መልኩ ለመተግበር እድል መፈጠሩን ነው ገዥው ያብራሩት።

በዚህም የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን፣ በየዘርፉ ተጨባጭ እድገት ማስመዝገብን፣ መዋቅራዊ ሽግግር ማምጣት እና ለአምራች ዘርፍ በቂ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እንዲኖር ማድረግ እንደ ግብ መያዙን አመልክተዋል።

በዚህ ሂደት የዓለም ባንክን ጨምሮ የልማት አጋሮች የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለማሳካት የሚደረገውን ጥረት በተለያየ መልኩ እንደሚደግፉ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት አዲሱ የዓለም ባንክ ፕሬዝዳነት አጃይ ባንጋም  ለኢትዮጵያ የልማት ግቦች መሳካት ባንኩ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል ነው ያሉት።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነሐሴ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው 13ኛ መደበኛ ስብሰባው የባንክ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ለማድረግ የቀረበውን ረቂቅ ፖሊሲ አጽድቆ በስራ ላይ እንዲውል መወሰኑ ይታወቃል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔውን ባሳለፈበት ወቅት የባንክ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ማድረግ “አገልግሎቶች በእውቀት እና በቴክኖሎጂ ለመደገፍ፣ የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር የበለጠ እንዲተሳሰር ለማድረግ ያስችላል” ማለቱም አይዘነጋም።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም