ቀጥታ፡

የህብረት ስራ ማህበራት የዜጎችን ፍትሃዊ  ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ  አበርክቶአቸው እየጨመረ መጥቷል

ድሬደዋ ፤ሐምሌ 26/2015  (ኢዜአ):- የህብረት ስራ ማህበራት የዜጎችን ፍትሃዊ  ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ  አበርክቶአቸው እየጨመረ መምጣቱን ተመለከተ።

የህብረት ስራ ማህበራት የዜጎችን ፍትሃዊ  ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል እያበረከቱት የሚገኙት አበረታች ስራዎችን በማጠናከር የተጀመረውን የብልፅግና ስኬታማ ጉዞ ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ መረባረብ እንደሚገባ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ተናገሩ።

የህብረት ስራ ማህበራት አጋርነት ለዘላቂ ልማት በሚል መሪ ሃሳብ አለምአቀፍ  የህብረት ስራ ማህበራት ቀን በድሬደዋ እየተከበረ ይገኛል።

በአለም አቀፍ ደረጃ ለ101ኛ ጊዜ በአገራችን ደግሞ ለ15ተኛ ጊዜ እየተከበረ በሚገኘው ቀን ላይ የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ እንደተናገሩት ፤ የህብረት ስራ ማህበራት ለግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምርና ለተጀመረው የግብርናው ዘርፍ አበረታች ጉዞ ስኬት ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ናቸው።

ይበልጥኑ የዜጎችን ፍትሃዊ እና እኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል እያበረከቱት የሚገኙት አስተዋጽኦ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ገልጸዋል ።

የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽነር ጌታቸው መለስ ዶክተር  እና የግብር ሚኒስትር ደኤታ ሶፊያ ካሳ ዶክተር  መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን እስከ ነገ በሚቀጥለው ስብሰባ በአገር አቀፍ ደረጃ የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎች የሚቀመሩበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ።

በአገር አቀፉ የህብረት ስራ ማህበራት አለምአቀፋዊ ቀን ላይ ከመላው ከፌደራልና  አገሪቱ የተገኙ የዘፈርፉ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም