ፍትህ ሚኒስቴር እና አሊያንስ ኦፍ ዘ ፒፕልስ ኦፍ ዘወርልድ በጋራ ለመስራት ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ፍትህ ሚኒስቴር እና አሊያንስ ኦፍ ዘ ፒፕልስ ኦፍ ዘወርልድ በጋራ ለመስራት ተስማሙ
አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 25/2015(ኢዜአ):-ፍትህ ሚኒስቴር እና አሊያንስ ኦፍ ዘ ፒፕልስ ኦፍ ዘወርልድ ከተሰኘ ተቋም በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የተፈራረሙት በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግስት የሕግ እና ፍትህ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለምአንተ አግደው እና የተቋሙ የኢትዮጵያ እና የመስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ተወካይ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት ስዩም ናቸው።
ስምምነቱ የፍትህ ሚኒስቴርንና የክልል ፍትሕ አካላትን የሕግ ማስከበርና የወንጀል መከላከል አቅም ለመገንባትና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማጠናከር፣የሰብአዊ መብት አያያዝና ክትትልን ለማሻሻል፣ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፣ፍትሕ ቢሮዎች እና የምርመራ ክፍሎችን የቢሮና የስራ አቅም ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተገልጿል።
በተጨማሪም የልምድ ልውውጦችን ለማድረግና ተሞክሮዎችን ለመጋራት፣የአጭርና የረዥም ጊዜ የትምህርትና ስልጠና መርሐ-ግብሮችን ለመተግበር የሚያግዙ የሙያ፣ የአይነት ድጋፍና ትብብር ለማድረግ እንደሚያስችልም ከሚኒስቴሩ ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።