ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የመዲናዋ ነዋሪዎች የቤት ጣሪያና ግድግዳ ግብር ክፍያቸውን እስከ ነሐሴ 30 እንዲያጠናቅቁ አሳሰበ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 25/2015 (ኢዜአ)፡- የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የመዲናዋ ነዋሪዎች የቤት ጣሪያና ግድግዳ ግብር ክፍያቸውን እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም እንዲያጠናቅቁ አሳሰበ።

የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አደም ኑሪ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በቤት ወይም በከተማ ቦታ ኪራይ እና የቤት ግብር አዋጅ መሰረት የጣራ እና ግድግዳ የግብር ክፍያ ሲተገበር መቆየቱን ጠቅሰዋል።

በተጠናቀቀው በጀት አመት አዲስ የገበያ ጥናት በማድረግ በሚያዝያ ወር ላይ ወቅታዊ የማድረግ ስራ መሰራቱን አስታውሰዋል።

በዚህም መሰረት እንዲከፍሉ ይጠበቅባቸው የነበሩ ሰዎች እስካሁንም በመክፈል ላይ መሆናቸውን ገልጸው ከሚጠበቀው አንጻር በርካቶች ገና ናቸው ብለዋል።

በአዲሱ ጥናት መሰረት ለመኖሪያ ቤት 50 በመቶ እንዲሁም ለድርጅት 75 በመቶ እንዲከፍሉ መወሰኑን አስታውሰዋል።

በጥናቱ መሰረት 800 ሺህ የሚጠጋ ግብር ከፋይ ይጠበቃል ያሉት ኃላፊው በአዲሱ ስሌት መሰረት እስካሁን 223 ሺህ ብቻ መክፈላቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ቁጥሩ ከፍ ያለ ግብር ከፋይ እስካሁን አለመክፈሉን በመጥቀስ ነዋሪዎች የቤት ጣሪያና ግድግዳ ግብር ክፍያቸውን እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም እንዲያጠናቅቁ አሳስበዋል።

ከዚህ ካለፈ ግን በህጉ መሰረት ተጨማሪ የቅጣት ክፍያ የሚከፍሉ መሆኑን አስረድተዋል።

በህጉ መሰረትም ከተቀመጠው ጊዜ ውጭ የሚመጡ ግብር ከፋዮች ባልተከፈለው ግብር መጠን 5 በመቶ ቅጣት የሚጠብቃቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይም የትልልቅ ህንጻ ባለቤቶች ግብር የመክፈል አዝማሚያ እስካሁን ዝቅተኛ ነው ያሉት ሃላፊው በተሰጠው ጊዜ በመክፈል ግዴታቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም