ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ፈተናዎችን የሚቋቋም ኢኮኖሚ በመገንባት ረገድ እያከናወነችው ያለው  ተግባር የሚደነቅ ነው-የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 25/2015 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ዓመታት  ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ጫናዎችን የሚቋቋም ኢኮኖሚ በመገንባት ረገድ እያከናወነችው ያለው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋ ገለጹ።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ፣ የብሔራዊ ባንክ ፕሬዝዳንት ማሞ ምህረቱና ሌሎች አመራሮች በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ከሚገኙት የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት አጃይ ባንጋ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

ውይይቱ በኢትዮጵያና በተቋሙ መካከል ባሉ የጋራ ጉዳዮች፣ ኢትዮጵያ በሁለተኛው የሀገር በቀለ የኢኮኖሚ ሪፎርም ቅድሚያ በምትሰጣቸው የልማት መስኮች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።

የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት አጃይ ባንጋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ውይይቱ ውጤታማና በቀጣይ አብሮ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ የላቀ ትብብር ለማድረግ መግባባት የተፈጠረበት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በብዙ ጫናዎች ውስጥ ሆና ተስፋ ሰጪ የልማት ስራዎች ማከናወኗን በጉብኝታቸው እንደተመለከቱ ከውይይቶች እንደተረዱ ገልጸዋል።

በተለይም እንደ ጎርፍ፣ ድርቅ፣ የኮሮና ወረርሽኝ፣ ግጭትና ሌሎችም ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮችን በመቋቋም ህዝብን በማስተባበር ለጫናዎች የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ያደረገችውን ጥረት አድንቀዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም ዓለም ፈተና ላይ መሆኑን በመጥቀስ ኢትዮጵያም የዚሁ አካል በመሆኗ ችግሮችን በራስ አቅም ለመሻገር የሚደረጉ ጥረቶች ሊበረታቱ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለዓለም  ባንክ ቁልፍ ሀገር ናት ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ባንኩ በቀጣይ ዓመታትም ከኢትዮጵያ ጋር በፋይናንስ፣ በሙያዊ ድጋፍና ሌሎችም አጋርነቶችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።


 

የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በበኩላቸው የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ቁልፍ አጋር መሆኑን  በመጥቀስ፤ ከፕሬዝዳንቱ ጋር በተደረገው ውይይትም ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ጫናዎችን በመቋቋም እየተመዘገቡ ስላሉ ኢኮኖሚያዊ ውጤቶች ማብራሪያ እንደተሰጣቸው ጠቅሰዋል።

በተለይም በመጀመሪያው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም የብዝሃ ኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዘዋወር የተጀመሩ ሂደቶችን፣ የፋይናንስ ዘርፍን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎችን በሚመለከትም ገለጻ እንደተረገላቸው ተናግረዋል፡፡

ውይይቱ ውጤታማ ነበር ያሉት ሚኒስትሩ ባንኩ በቀጣይ ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለማምጣት፣ ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር ለመፍጠር፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና የመንግሥት አገልግሎትን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት እገዛ እንዲሚያደርግ ማረጋገጡን ገልጸዋል። 

ባንኩ በኢትዮጵያ በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት የሚደረጉ ጥረቶችን ለማገዝ እና የተጀመሩ የገጠርና የከተማ ልማት ፕሮጀክቶችን የገንዘብ ድጋፍ ለማስቀጠል መግባባት ላይ መድረሱንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ በሚከናወኑ የልማት ተግባራት ላይ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጡን ጠቅሰው፤ የዕዳ ቅነሳን በሚመለከት  ከሌሎች አበዳሪ ተቋማት ጋር በመተባበር ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚሆን ማረጋገጡን ጠቅሰዋል። 

አጃይ ባንጋ በዛሬው ዕለት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጋር በመሆን በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኙትን ጄይ ጄይ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ እና ሱፍሌ የብቅል ፋብሪካን መጎብኘታቸው ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም