ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት በማሻሻልና የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ረገድ ስኬት ተመዝግቧል - የከተማ አስተዳደሩ ዋና ስራ አስኪያጅ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 25/2015 (ኢዜአ)፡- በአዲስ አበባ የነዋሪዎችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማሻሻልና የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ረገድ ስኬቶች መመዝገቡን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስኪያጅ ጥራቱ በየነ ገለጹ።

የከተማ አስተዳደሩ ስራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት በ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

የአስተዳደሩ ዋና ስራ አስኪያጅ ጥራቱ በየነ፤ የበጀት ዓመቱን አጠቃላይ ክንውንና የተገኙ ውጤቶችን አስመልክቶ ባደረጉት ገለጻ የነዋሪዎችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ  የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

የሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እና በከነማ ፋርማሲ ድርጅት ላይ የተደረገውን ሪፎርም ስኬት ከተገኘባቸው ተቋማት መካከል እንደሚጠቀሱ ተናግረዋል።

በተቋማቱ የሰው ኃይል አቅምን በማሳደግና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር በመዘርጋት ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት መቻሉን አመልክተዋል።

በዚህም በመዲናዋ የመታወቂያ አገልግሎት ካገኙ 784 ሺህ ዜጎች መካከል 90 በመቶው የዲጂታል አገልግሎት ማግኘታቸውንም ነው አቶ ጥራቱ የጠቀሱት።

በከነማ ፋርማሲዎች አማካኝነት በተመጠጣኝ ዋጋ መድኃኒት መቅረቡንና በዚህም 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ25 በላይ አዳዲስ የውሃ ጉድጓዶችን በመቆፈር በየቀኑ ከ68 ሺህ ሜትሪክ ኪዩብ በላይ ውሃ ተደራሽ ማድረግ ተችሏልም ነው ያሉት።

በመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ለሕብረተሰቡ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ የመስጠትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት የቀጣይ ትኩረት ሆኖ የሚሰራበት መሆኑንም ገልጸዋል።

የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተክሌ ኢዲዱ፤ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ቅሬታ ከሚነሳባቸው ተቋማት መካከል እንደነበር አስታውሰው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ አሰራሩን ማሳለጥ መቻሉን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ሞገስ አርጋው፤ የውሃ የተደራሽነትና የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ትኩረት ተሰጥቶ መከናወኑን ተናግረዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም