የሃይማኖት አባቶች ዜጎችን በስነ-ምግባር በመቅረጽ ለሰላምና አብሮነት መጎልበት ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሰላም ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የሃይማኖት አባቶች ዜጎችን በስነ-ምግባር በመቅረጽ ለሰላምና አብሮነት መጎልበት ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሰላም ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 25/2015 (ኢዜአ)፡- የሃይማኖት አባቶች ዜጎችን በስነ-ምግባር በመቅረጽ ለሰላምና አብሮነት መጎልበት ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሰላም ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና ከጅስራ ኮንሶርቲየም ፕሮጀክት ጋር በመተባበር " የሃይማኖት አስተምህሮ ለሰላም ግንባታ ያላቸው ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ ከሃይማኖት ተቋማት መሪዎች እና ምሁራን ጋር በአዲስ አበባ የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡
በዚሁ ወቅት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ ሰላም፣ ዕርቅ እና ይቅርታ የሁሉም ሃይማኖቶች መሰረት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የሃይማኖት አባቶች በስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ በመቅረጽ ሰላምና አብሮነት እንዲጎለብት በማድረግ ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ አኳያ የሃይማኖት አባቶች ሰላም እንዲሰፍን፣ መተባበር እንዲመጣ እና መከባበር እንዲሰርጽ የጀመሩትን ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የጂስራ ኮንሰርቲዬም ፕሮጀክት ዳይሬክተር መስፋን አበበ፤ የመድረኩ ዋነኛ ዓላማ ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ማህበረሰብን በመገንባት ረገድ ያላቸውን ሚና እንዲያጠናክሩ ለማድረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አባቶች በውስጣቸው የሚከሰቱ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ለማህበረሰቡ አርዓያ መሆን እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ የተሳተፉ የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው በሃይማኖት ተቋማት መካከል መግባባት፣ መከባበር እና መተባበር እንዲኖር መድረኩ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
በመንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ጽሀፈት ቤት የስብከተ ወንጌል እና ሃዋሪያዊ ተልዕኮ መምሪያ ዋና ሃላፊ መልዕከ ሰላም ዶክተር አባ ቃለጽድቅ ሙሉጌታ፤ ከሃይማኖታዊ አስተምህሮ ውጪ የህዝቦችን አብሮነት የሚሸረሽሩ መልዕክት የሚያስተላልፉ አካላትን በጋራ ማስተካከል እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የትምህርት ክፍል ኋላፊ አባ ዳንኤል ሃሶ በበኩላቸው የተለያዩ ሃይማኖት የሚከተሉ አባቶች አንድ በሚያደርጋቸው ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
ቤተ-እምነቶች እርስ በእርስ እንዲከባበሩ እና እንዲተባበሩ ለማስቻልም መቀራረብና መወያየት ይገባል ነው ያሉት፡፡
ከዚህ አኳያ መድረኩ በሃይማኖት ተቋማት መካከል ያለው ትብብር እንዲጎለብት በማድረግ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የልማትና ተራድኦ ዘርፍ ሃላፊ ሼህ ዛኪር ኢብራሂም እና የገሊላ ኢንተርናሽናል ሴሚናርየም ፕሬዚዳንት ዶክተር ጥላዬ ደመቀ በሰጡት አስተያየት ሁሉም ቤተ እምነቶች በዜጎች መካከል ሰላምና አብሮነት እንዲጎለብት ማስተማር እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
በመድረኩ ከሁሉም የሃይማኖት ተቋማት የተውጣጡ አባቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡