ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሴካፋ ከ18 ዓመት የሴቶች እግር ኳስ ውድድር በጎል የተንበሸበሸ ድል አስመዘገበች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2015(ኢዜአ):- በምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት(ሴካፋ) ከ18 ዓመት በታች የሴቶች የእግር ኳስ ውድድር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዛንዚባር አቻውን 6 ለ 1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል።

በቻማዚ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ የአጥቂ መስመር ተሰላፊዋ እሙሽ ዳንኤል ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርታለች።

ማህሌት ምትኩ ሁለት ግቦችን ስታስቆጥር ቀሪዋን ግብ ትንቢት ሳሙኤል ከመረብ ላይ አሳርፋለች።

ሀዋ ጁማ ለዛንዚባር ብቸኛዋን ግብ አስቆጥራለች።

በአሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ የሚመራው ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ ሁለተኛ ድሉን አስመዝግቧል።

የዛሬውን ጨዋታ ተከትሎ ብሔራዊ ቡድኑ በውድድሩ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች አጠናቋል።

ቡድኑ ከዚህ ቀደም ብሩንዲ 2 ለ 0 ያሸነፈ ሲሆን በዩጋንዳ እና ታንዛንያ መሸነፋቸው ይታወቃል።

በሌላኛው የውድድሩ መርሐ-ግብር ዩጋንዳ ከብሩንዲ ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

ኬንያ እና ሩዋንዳ ከውድድሩ ራሳቸውን ማግለላቸውን ተከትሎ ሴካፋ የውድድሩን ፎርማት በመቀየር አምስቱ አገራት እርስ በእርሳቸው የሚጫወቱበትን አማራጭ (round robin format) ለመጠቀም ተገዷል።

በእርስ በእርስ ጨዋታው የተሻለ ውጤት ያስመዘገበው አገር የውድድሩ አሸናፊ ሲሆን ሌሎቹ አገራት እንደ ውጤታቸው ደረጃቸውን ያገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም