ቀጥታ፡

ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ የኢንቨስትመንት ማሻሻያዎች እንደሚደግፍ ገለጸ 


አዲስ አበባ ሐምሌ 25/2015(ኢዜአ):-  ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC)
በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ የኢንቨስትመንት ማሻሻያዎች እንደሚደግፍ አስታወቀ። 
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ ከኮርፖሬሽኑ ቀጣናዊ ዳይሬክተር ማሪ ፖርተር ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

በውይይቱ ኮሚሽኑና ኮርፖሬሽኑ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን ማስተዋወቅ እና አገሪቷ ሙሉ የኢንቨስትመንት አቅሟን መጠቀም በምትችልበት ሁኔታ ላይ በትብብር መስራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ኮርፖሬሽኑ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ማሻሻያ ጉዞ ድጋፉን እንደሚያደርግም ኮሚሽነር ለሊሴ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ ገልጸዋል።


 

የዓለም ባንክ ግሩፕ እህት ድርጅት እና አባል የሆነው የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን እ.አ.አ 1956 የተቋቋመ ሲሆን ዋና መቀመጫው በዋሺንግተን ዲሲ ነው።

ኮርፖሬሽኑ በማደግ ላይ በሚገኙ አገራት የግሉ ዘርፍ የልማት ተሳትፎ እንዲያድግ የሚያበረታቱ የኢንቨስትመንት ማማከር እና የንብረት ሀብት አስተዳደር አገልግሎቶችን መስጠት ዋንኛ አላማው አድርጎ ይሰራል።

ኮርፖሬሽኑ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በማደግ ላይ በሚገኙ አገራት በዘላቂ ግብርና፣ጤና፣ ትምህርት፣የፋይናንስ ተደራሽነት እና የመሰረተ ልማት ግንባታ አስመልክቶ የልማት ግቦች በመቅረጽ ድጋፍ ያደርጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም