ቀጥታ፡

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ከዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 25/2015(ኢዜአ):- የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ከሚገኙት የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋን ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

ውይይቱ በኢትዮጵያና በዓለምን ባንክ መካከል መልካም ግንኙነት ይበልጥ መጠናከር በሚችልበት ሁኔታ እንዲሁም የኢትዮጵያ ቅድሚያ በምትሰጣቸው የልማት መስኮች ላይ ያተኮረ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።

አቶ አህመድ ሺዴ በዓለም ባንክ የሚደገፉ ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ ለዋንኞቹ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ጠቅሰው በኢትዮጵያና በዓለም ባንክ መካከል ያለው የልማት ትብብር ዘላቂና አካታች እድገት ለማስመዝብ እንደሚያግዝም አመልክተዋል።


 

በተሻሻለ ምርታማነትና በተወዳዳሪነት መንፈስ ኢኮኖሚያዊ ሽግግርን ለማፋጠን የታቀደውን ሁለተኛውን የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ሊያጋጥሙ ስለሚችሉት መልካም እድሎችና ፈተናዎችን በተመለከተ ሚኒስትሩ ለፕሬዝዳንቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ የልማት ፍላጎትን ከማክሮ ኢኮኖሚ ተግዳሮቶች አንጻር አገሪቱ ግዙፍ የሆነውን ማሻሻያ አጀንዳ ውጤታማ በሆነ መልኩ ተግባራዊ እንድታደርግ የዓለም ባንክ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

አቶ አህመድ ጨምረውም ድህነት እያስከተለ ያለውን ልዩ ተግዳሮት ታሳቢ ያደረገ ምላሽ ከባንኩ የማሻሻያ ሂደት በተለይም የባንኩ ድጋፍ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው አገራት አንገብጋቢ ፍላጎት ጋር መጣጣሙን በተመለከተ ለውጥ እንሚጠብቁም ነው የተናገሩት።

አጃይ ባንጋ ባንኩ ባካሄደው የለውጥ ሂደት በአጭር ጊዜ ውስጥ ላበረከቱት አስተዋጽኦና የባንኩን የፋይናንስ አቅም ለማሳደግ በቅርቡ ለተወሰዱ ውጤታማ እርምጃዎች ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም