የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆን ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል- የባንኩ ፕሬዚዳንት አጃይ ባንጋ - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆን ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል- የባንኩ ፕሬዚዳንት አጃይ ባንጋ
አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 25/2015(ኢዜአ):- የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆን እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የባንኩ ፕሬዚዳንት አጃይ ባንጋ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እና የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋ የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክን በመጎብኘት በፓርኩ ቅጥር ግቢ የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
ከጉብኝቱ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ በጉብኝታቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለበርካታ ወጣቶች በተለይም ለሴቶች የስራ እድል መፍጠር እንደቻሉ መመልከታቸውን ገልጸዋል።
ይህ ደግሞ ለሴቶችና ወጣቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።
የዓለም ባንክ ከኢንዱስትሪ ጋር የተያያዙ ስራዎችን በመደገፉ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አያይዘውም የዓለም ባንክ ለኢትዮ-ጅቡቲ የመንገድ ማሻሻያ ግንባታ ያደረገውን የፋይናንስ ድጋፍ አንስተዋል።
የመንገድ ማሻሻያ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያና በጅቡቲ ላሉ ስራ ፈጣሪዎች የገቢና ወጪ ንግድ ሎጂስቲክስን በማሳለጥ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
አክለውም መንግስት የሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶች እሴት በመጨመር ወደ ውጭ ለመላክ እያደረገ ያለው ጥረት በርካታ የስራ እድል ከመፍጠር በላይ ለአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለዋል።
በመሆኑም የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆን እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ አጋር መሆኑን አንስተው በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በማህበራዊ፣ በዲጂታል ዘርፍ እና ሌሎች የልማት መስኮች እየተሳተፈ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ እድገቷን ለማስቀጠል የተለያዩ የግሉ ዘርፍ ተቋማትን በኢኮኖሚው ማሳተፏን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አንስተዋል።
የተጀመሩ ሀገራዊ የለውጥ ስራዎችን በማስቀጠል እንዲሁም ሰላምና አንድነትን በማስጠበቅ ሁለንተናዊ ልማትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።