አዲስ አበባን ውብና ሁሉን አቀፍ እድገት የተረጋገጠባት ከተማ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት በአረንጓዴ ልማት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ-የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባን ውብና ሁሉን አቀፍ እድገት የተረጋገጠባት ከተማ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት በአረንጓዴ ልማት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ-የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ
አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 25/2015(ኢዜአ):- አዲስ አበባን ውብና ሁሉን አቀፍ እድገት የተረጋገጠባት ከተማ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት በአረንጓዴ ልማት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ ገለጹ።
ኃላፊው በመዲናዋ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ17 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተከላ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 25 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ተጠናቆ ሁለተኛው ምእራፍ በመከናወን ላይ ይገኛል።
የሁለተኛውን ምዕራፍ አረንጓዴ ልማት "ነገን ዛሬ እንትከል" በሚል መሪ ሃሳብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም በአፋር ክልል ተጀምሮ በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች የችግኝ ተከላው በማካሄድ ላይ ነው።
በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለውን የአረንጓዴ ልማት በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ፤ ኢትዮጵያ ለአካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።
የአረንጓዴ ልማቱ ከተሞችን ጨምሮ በሁሉም አካባቢዎች እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው በአዲስ አበባ ባለፉት አራት ዓመታት በተደረገው የችግኝ ተከላ የከተማዋን አረንጓዴ ልማት 15 በመቶ ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል።
በመሆኑም አዲስ አበባን የተዋበችና ሁሉን አቀፍ እድገት የተረጋገጠባት ከተማ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት በአረንጓዴ ልማት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ከተማዋን አረንጓዴና ውብ ለማድረግ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለመስህብ ስፍራ ምቹነትና ለአየር ሁኔታ የአረንጓዴ ልማቱ የላቀ ሚና ያለው መሆኑንም አብራርተዋል።
በሁለተኛው ምእራፍ የአረንጓዴ ልማት ስኬትም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሞገስ፤ ዘንድሮ 17 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ እስካሁን የአብዛኛው ችግኝ ተከላ ተከናውኗል ብለዋል።
እስካሁንም ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ተክሎች፣ ለመድሃኒትነት የሚውሉና ለከተማ ውበት የሚያገለግሉ ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩን ለማሳካት ተቋማት፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮች እና አጠቃላይ የነዋሪውን ተሳትፎ በማድነቅ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።