በ6ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና የማለፊያ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች በድጋሚ የሚማሩበት ሥርዓት ተዘጋጅቷል - የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ

አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 25/2015(ኢዜአ):- በ6ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና የማለፊያ ውጤት ያላስመዘገቡ ተማሪዎች በድጋሚ የሚማሩበት ሥርዓት መዘጋጀቱን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።

በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሰረት ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠው የ6ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና  ውጤት ይፋ ሆኗል።

ውጤቱንም በማስመልከት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፤ ፈተናውን የወሰዱ ተማሪዎች 73 ሺህ 667 ሲሆኑ የማለፊያ ነጥብ ያስመዘገቡ 56 ሺህ 842 ተማሪዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

3 ተማሪዎች 99 ከመቶ አማካይ ውጤት ማምጣታቸውን ገልጸው 477 ተማሪዎች ደግሞ ከ95ከመቶ በላይ ማስመዝገባቸውን ጠቁመዋል።

104 ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ሙሉ በሙሉ ማሳለፍ መቻላቸውን ተናግረዋል።

የማለፊያ ውጤት ለመደበኛ 50 እና ከዛ በላይ ሲሆን ለአካል ጉዳተኞች 45 እና ከዛ በላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ተማሪዎች ውጤታቸውን በተቋሙ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ በሚገኘው ማስፈንጠሪያ በመግባት መመልከት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

ውጤት ያልመጣላቸው ተማሪዎች በድጋሚ የሚማሩበት ሥርዓት መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

እንዲሁም ወደ ሌላ ትምህርት ቤት ተዘዋውረው መማር የሚፈልጉ ተማሪዎች በዝውውር መመሪያ መሰረት እንደሚስተናገዱ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠው የ6ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና ከ1987 ዓ.ም በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ዓመት መሰጠቱ ይታወሳል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም