ቀጥታ፡

የተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና እየተሰጠ ነው

ነቀምቴ/አምቦ/ሰመራ (ኢዜአ) ሐምሌ 25/2015፡-የተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች መሰጠት ተጀምሯል።

ፈተናው በወለጋ፣ በአምቦና በሰመራ ዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጠ ነው።

በወለጋ ዩኒቨርሲቲ በ2ኛ ዙር የሚፈተኑ የተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ ተፈታኝ ተማሪዎች በዛሬው እለት ፈተናውን መጀመራቸውን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር መልካ ሂካ እንዳሉት በዚህ ዙር በነቀምቴ ካምፓስ 10 ሺህ 986፣ በጊምቢ ካምፓስ 1ሺህ 779 ተማሪዎች እንዲሁም በሻምቡ ካምፓስ 2ሺህ 220 ተማሪዎች ፈተናውን ይወስዳሉ።


 

በሦስቱም የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ካምፓሶች የ12ኛ ክፍል አገር-አቀፍ ማጠቃለያ ፈተና የ2ኛው ዙር የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች በመርሃ ግብሩ መሠረት በእንግሊዘኛ ትምህርት ፈተና ተጀምሯል። 

ተማሪዎች በተረጋጋና በጥሩ ስነ ምግባር እየወሰዱ መሆናቸውንም ዶክተር መልካ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ አምቦ ዩኒቨርሲቲ  18 ሺህ103 የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች የዘንድሮ 12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና  መውሰድ መጀመራቸው ተገልጿል።

የአምቦ ዩኒቨርሲተ ህዝብ ግንኙነት ዳሬክተር ዶክተር መንግስቱ ቱሉ እንደገለጹት ለፈተናው ስኬት ከዩኒቨርሲቲውና ከጸጥታ አካላት እንዲሁም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ ነው።

ፈተናው ያለምንም ችግር በሰላማዊና በተረጋጋ ሁኔታ እየተሰጠ መሆኑን አክለዋል።

በአንደኛው ዙር  16ሺህ 846 የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ያለምንም ችግር ተፈትነው ማጠናቀቃቸውንም ተናግረዋል።

በዩኒቨርስቲው ዋና ጊቢ ጨምሮ ሀጫሉ ሁንዴሳ ካምፓስና በጉደር ማሞ መዘምር ካምፓስ እንዲሁም ወሊሶ ካምፓሶች ተማሪዎች ፈተናውን እየወሰዱ ነው ብለዋል።

በአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ የፈተና ቡድን መሪ የሆኑት አቶ መሐመድ ሰይድ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች በሠመራ ዩኒቨርሲቲም ፈተናውን መውሰድ መጀመራቸውን ገልፀዋል።

ዩኒቨርሲቲው የ2ኛው ዙር የተፈጥሮ ሣይንስ ተማሪዎችን ለማስፈተን ለተከታታይ ሁለት ቀናት ሲቀበል መቆየቱን ገልፀው በዛሬው ዕለት ፈተናው መጀመሩን አስታውቀዋል።

የፈተናዎች ቡድን መሪው አቶ መሐመድ ለኢዜአ እንደገለፁት ፈተናውን ለማከናወን ያስችል ዘንድ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የተለያዩ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አስረድተዋል።

በሁለተኛው ዙር ፈተናውን የሚወስዱት ተማሪዎች በክልሉ ውሰጥ ከሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ከ41 ትምህርት ቤቶች የመጡ መሆናቸውንም ገልጸዋል። 

አቶ መሃመድ አያይዘው እንዳስታወቁት በተፈጥር ሳይንስ 3ሺህ 603  ተፈታኞች የተዘጋጁ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 1ሺህ 308 ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ በክልሉ ፈተናው የሚወሰዱት 5ሺህ 984 ተማሪዎች መሆናቸው ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም