የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የተፈጥሮ ሀብትን ለመንከባከብ የሚያግዝ ልማት እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የተፈጥሮ ሀብትን ለመንከባከብ የሚያግዝ ልማት እየተካሄደ ነው
ጎንደር፤ ሐምሌ 25 / 2015 (ኢዜአ) ፡- የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን ስነ-ምህዳር በመጠበቅ የተፈጥሮ ሀብቱን ለመንከባከብ የሚያግዝ ልማት እየተካሄደ መሆኑን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
በክረምቱ ከ20 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞች መተከላቸውን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል፡፡
የጽህፈት ቤቱ ተወካይ አቶ ኤፍሬም ወንዴ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ችግኞቹ በተያዘው የክረምት ወቅት በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራና በመደበኛው መርሃ ግብር የተተከሉ ናቸው፡፡
ችግኞቹ 5 ሄክታር በሚሸፍነው በፓርኩ ክልል አዲስጌ በተባለው አካባቢ መተከላቸውን ጠቅሰው፤ ይህም በፓርኩ ደርሶ በነበረ የእሳት ቃጠሎ የወደሙ ደኖችን መልሶ ለመተካት እንደሚያግዝ አስረድተዋል።
በአካባቢው ህብረተሰብ ተሳትፎና በችግኝ ክብካቤ ሙያ በሰለጠኑ ባለሙያዎች ከተተከሉ ሀገር በቀል ችግኞች መካከልም ግራር፣ ወይራ፣ ኮሶና "ውጨና " ዝርያዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡
የችግኝ ተከላ ስራውና ልማቱ እስከ ቀጣዩ ነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም መግቢያ እንደሚቀጥል ጠቁመው፤ ከ30 ሺህ በላይ ችግኞችን በመትከል 10 ሄክታር የፓርኩን ክልል በደን ለመሸፈን መታቀዱን ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል በዘመቻ መልክ ሲከናወን የቆየው የችግኝ ተከላና ክብካቤ ስራ ውጤታማ ባለመሆኑ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ስልጠና በወሰዱ የአካባቢው አርሶ አደሮች በመከናወኑ ውጤት ማምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም ባለፈው ዓመት በ5 ሄክታር መሬት ላይ ከተተከሉ 25 ሺህ ችግኞች ውስጥ 85 በመቶ መጽደቁን አመልክተዋል፡፡
የፓርኩን ስነ-ምህዳር በመጠበቅ በኩል ሀገር በቀል ችግኞች የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ በሳይንሳዊ ጥናት በተደገፈ የክብካቤ ስራ ይከናወናል'' ያሉት የፓርኩ የደን ልማት ባለሙያ አቶ ታደሰ ይግዛው ናቸው፡፡
የችግኝ ተከላ ስራው በፓርኩ የሚገኙ የዱር እንስሳት አመቺ መጠለያ እንዲኖራቸው በማድረግና የመኖ አቅርቦት እጥረቱንም በማቃለል ረገድ የጎላ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በመንግስትና በህብረተሰቡ የጋራ ጥረት 70 በመቶ የሚሆነውን የፓርኩን ክልል ከቤት እንስሳት ልቅ ግጦሽ ነጻ በመደረጉ የፓርኩን የተፈጥሮ ሀብት ለመጠበቅ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አስታውሰዋል፡፡
በችግኝ ክብካቤ ስራው እየተሳተፉ የሚገኙት አርሶ አደር ሞላ ግዛቸው በሰጡት አስተያየት፤ ፓርኩ የህልውናችን መሰረት በመሆኑ የተተከሉ ችግኞች ፀድቀው ለውጤት እንዲበቁ እየተንከባከብን ነው ብለዋል፡፡
የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ ዋልያ፤ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ ሌሎችም ብርቅዬ የዱር እንስሳትና አእዋፋት መገኛ ሲሆን 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት እንዳለው መረጃዎች ያመለክታሉ።