ቀጥታ፡

የኢትዮጵያንና ዮርዳኖስን ለረጅም ጊዜ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባ ተገለፀ 

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 25/2015 (ኢዜአ)፦ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ ኤዥያና ፓስፊክ ዳይሬክቶሬት ጄነራል አምባሳደር ገበየሁ ጋንጋ ከዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር አምባሳደር ጃነቲ ማሚላ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡

በአምባሳደር ገበየሁ ጋንጋ የተመራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ልዑክ  በዮርዳኖስ  የስራ ጉብኝት እያደረገ ነው። 

በውይይቱ ወቅት አምባሳደር ገበየሁ ኢትዮጵያና ዮርዳኖስ ለረጅም ጊዜ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው አገራት መሆናቸው ገልጸው ግንኙነቱን ለማሳደግ ያለውን ሠፊ ዕድል መጠቀም እንደሚገባ አስገንዘባዋል፡፡ 

በዚህም በንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም መስኮች ሥምምነት ማድረግ፣ የከፍተኛ ባለስልጣናት ጉብኝት፣ በቅርቡ የተፈረመውን የሥራ ስምሪት ወደ ተግባር ማስገባት ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት ወደ ጆርዳን የሚያደርገውን በረራ በሳምንት ከአራት ወደ አምስት ለማሳደግ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በኩል ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

አምባሳደር ጃንቲ በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የንግድና ቱሪዝም ግንኙነቱን ማጠናከር የሚያስችል  ስምምነት ለመፈራረም ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅሰው ረቂቅ ስምምነቶችን አዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲያቸው በኩል እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ጆርዳን የቀጥታ በረራ ማካሄድ መጀመሩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን የሚያጠናክር በመሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም የዮርዳኖስ መንግስት አገሪቱን በህክምና ቱሪዝም ተመራጭ መዳረሻ ለማድረግ እየሰራ መሆኑነ ገልጸው ፤ በዚህም ለሁለቱ አገሮች ተጨማሪ የትብብር መስክ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ 

የልዑካን ቡድኑ አማን ከሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዮርዳኖስ አካባቢ ተወካይ አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ ጋር በመሆን ጽህፈት ቤቱ ከዮርዳኖስ የኢትዮጵያ ክብር ቆንስላ ጋር በመተባበር የቱሪዝም፣ ንግድ እና ኢንቨስትምነት ፕሮሞሽን ስራዎች ለመስራት እና አየር መንገዱ ወደ አማን በማድረግ ላይ ባለው በረራ ዙሪያ ውይይት ማካሄዳቸው ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም