ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሴካፋ ከ18 ዓመት በታች የሴቶች የእግር ኳስ ውድድር ከዛንዚባር ጋር ትጫወታለች

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 25/2015(ኢዜአ):-በምስራቅ እና መካከለኛ አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት(ሴካፋ) ከ18 ዓመት በታች የሴቶች የእግር ኳስ ውድድር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዛንዚባር ጋር ዛሬ ጨዋታውን ያደርጋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በታንዛንያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ያለው ውድድር ዛሬ ስምንተኛ ቀኑን ይዟል።

በውድድሩ ታንዛንያ፣ኢትዮጵያ፣ዩጋንዳ፣ዛንዚባር እና ብሩንዲ በመሳተፍ ላይ ናቸው።

ኢትዮጵያ በውድድሩ አራተኛ እና የመጨረሻ ጨዋታዋን ዛሬ ከዛንዚባር ጋር በቻማዚ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰአት ላይ ታደርጋለች።

በአሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ ለጨዋታው ትናንት በአሁሩ ስታዲየም ልምምዱን አድርጓል።


 

ቡድኑ ከዚህ ቀደም ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች በሁለቱ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ አሸንፏል።

በታንዛንያ እና ዩጋንዳ የተሸነፈ ሲሆን ከትናንት በስቲያ ብሩንዲን 2 ለ 0 ማሸነፉ ይታወቃል።

ተጋጣሚዋ ዛንዚባር በውድድሩ እስከ አሁን ባደረገቻቸው ሁለት ጨዋታዎች በታንዛንያ እና ዩጋንዳ ተሸንፋለች።

በሌላኛው መርሐ-ግብር ዩጋንዳ ከብሩንዲ በቻማዚ ስታዲየም ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ኬንያ እና ሩዋንዳ ከውድድሩ ራሳቸውን ማግለላቸውን ተከትሎ ሴካፋ የውድድሩን ፎርማት በመቀየር አምስቱ አገራት እርስ በእርሳቸው የሚጫወቱበትን አማራጭ (round robin format) ለመጠቀም ተገዷል።


 

በእርስ በእርስ ጨዋታው የተሻለ ውጤት ያስመዘገበው አገር የውድድሩ አሸናፊ ሲሆን ሌሎቹ አገራት እንደ ውጤታቸው ደረጃቸውን ያገኛሉ።

የሴካፋ ከ18 ዓመት በታች የሴቶች የእግር ኳስ ውድድር እስከ ነሐሴ 1/2015 ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም