ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የገቢ ምርት በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏል - የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

ሚዛን አማን ፤ ሐምሌ 24/2015 (ኢዜአ) በተጠናቀቀው 2015 በጀት አመት ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የገቢ ምርት በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ከክልሎች እና ተጠሪ ተቋማት ጋር በ2015 የስራ እቅድ አፈጻጸምና በ2016 እቅድ ላይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ እየመከረ ነው።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በምክክር መድረኩ  ላይ እንዳሉት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እንደ ሀገር በኢንዱስትሪው ዘርፍ በ2015 በጀት ዓመት መልካም የሚባል ውጤት ታይቷል።

በሁሉም ክልሎች በተደረገ ርብርብ 1 ሺህ የሚሆኑ አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉን አመልክተዋል።

እንዲሁም የማምረት አቅምን በ2014 በጀት አመት ከነበረው 52 በመቶ ወደ 55 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

በዚህም ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉን አስታውቀዋል።

የኢንዱስትሪ መስፋፋት የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን ጠቅሰው በተጠናቀቀው በጀት አመት በተደረገ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከ255 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ59 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ማቅረብ የተቻለ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ "ለ2016 በጀት  ዓመት መሠረት የሚሆን ሥራ በሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅት ተፈጽሟል " ብለዋል።

"የታየው ጅምር ውጤት እንደ ሀገር ከሚፈልገው የገበያ መጠን አንጻር ገና ብዙ ሥራ የሚጠይቅ በመሆኑ በ2016 በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ጥረት ይደረጋል" ሲሉም አክለዋል።

እንደ ሀገር በተለያዩ ክልሎች ያሉ ፀጋዎችን በመለየት ለየአካባቢው የሚሆኑ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎችን የማስፋፋት ሥራ በትኩረት እንደሚሰራ ሚኒስትሩ አመላክተዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ በርካታ ሀብቶች በክልሉ ውስጥ ቢኖሩም "እሴት ለመጨመር የሚያስችሉ ኢንዱስትሪዎች የሉም" ብለዋል።

በተለይ አርሶ አደሩ ከግብርና ምርቶች ማግኘት የሚገባውን ያህል ጥቅም እያገኘ አለመሆኑን ጠቅሰው የክልሉ መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር መፍትሄ ለማምጣት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ለግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ እምቅ ሀብቶች ያሉት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  የዞኑ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀበሌ መንገሻ ናቸው።

ሀብቶቹ ዕሴት ተጨምሮባቸው የተፈለገው ጥቅም በአምራቾችም ይሁን ሀገራዊ ኢኮኖሚ ላይ እንዲያሳርፍ ሚኒስቴሩ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

ባለሀብቶችም አካባቢው ያለውን አቅም ለመጠቀም በኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሰማሩ  ጥሪ አቅርበዋል።

በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ባለው የምክክር መድረክ ተጠሪ ተቋማትን ጨምሮ የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም