ለሸኔ የሽብር ቡድን የትጥቅ ድጋፍ ለማድረግ ሲጓዙ የነበሩ አራት ተጠርጣሪዎችን መያዙን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
ለሸኔ የሽብር ቡድን የትጥቅ ድጋፍ ለማድረግ ሲጓዙ የነበሩ አራት ተጠርጣሪዎችን መያዙን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ገለፀ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2015 (ኢዜአ):-ለሸኔ የሽብር ቡድን የትጥቅ ድጋፍ ለማድረግ ሲጓዙ የነበሩ አራት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ መነሻቸውን ከአዋሽ አድርገው በመንግሥት መኪና 2 ስናይፐር ፣ አንድ ላውንቸር፣ 5 የላውንቸር ተተኳሽ ቅምቡላ እና 28 የስናይፐር ካርታ ከመሰል ጥይት ጋር ይዘው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ገልጿል፡፡
በተጨማሪም 2 ሙሉ የመከላከያ ሠራዊት ዩኒፎርም፣ 3 ሙሉ የቀድሞ የአፋር ልዩ ኃይል ዩኒፎርም እና ሸሚዝ ጭነው ለሸኔ የሽብር ቡድን ለማድረስ ሲጓዙ ሰበታ ከተማ እንደደረሱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አመልክቷል፡፡
ሕብረተሰቡ መሰል የወንጀል ተግባራትን ሲመለከት ለፀጥታ አካላት በፍጥነት ጥቆማ በመስጠት እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ግብረ-ኃይሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡