ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ ጋር በትምህርት ዘርፍ ያላትን ትብብር ለማጠናከር ትሻለች - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ ጋር በትምህርት ዘርፍ ያላትን ትብብር ለማጠናከር ትሻለች - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2015(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ጥራት ያለውን ትምህርት ለማስፋፋት ከደቡብ አፍሪካ ጋር በትምህርት ዘርፍ ያላትን ትብብር ለማጠናከር እንደምትፈልግ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለፁ።
የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ (ዩኒሳ) የተመሠረተበት 150ኛ ዓመት በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው።
በመርሃ-ግብሩ የደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ግንኙነቶችና ትብብር ሚኒስትር ዶክተር ናሌዲ ፓንዶር ተግኘተዋል።
ዩኒሳ በኢትዮጵያና በደቡብ አፍሪካ መካከል የትምህርት አጋርነት እንዲጠናከር በተለይም ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጉ በመድረኩ ተገልጿል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዚሁ ጊዜ፤ ኢትዮጵያ ጥራት ያለው ትምህርት ለማስፋት ከደቡብ አፍሪካ ጋር በትምህርት ዘርፍ ያላትን ትብብር ለማጠናከረ ትፈልጋለች።
በዚህ ተለዋዋጭ ዓለም የኢትዮጵያ መፃዒ ዕጣ ፈንታ በተለይም ተወዳዳሪነቷ የሚወሰነው ጥራት ባለው ትምህርት መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም ኢትዮጵያ አበክራ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።
የደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ግንኙነቶችና ትብብር ሚኒስትር ዶክተር ናሌዲ ፓንዶር በበኩላቸው፤ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በትምህርት ዘርፍ ያላትን አጋርነት ታጠናክራለች ብለዋል።
በተለይም በጥናትና ምርምር፣ በልማትና በኢኖቬሽን መስክ አጋርነቱ ለማዳበር ይሠራል ነው ያሉት።