በሁለተኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባዔ ኢትዮጵያ በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ስኬታማ ሥራዎችን አከናውናለች - ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሣ - ኢዜአ አማርኛ
በሁለተኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባዔ ኢትዮጵያ በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ስኬታማ ሥራዎችን አከናውናለች - ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሣ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2015 (ኢዜአ) ፡- በሁለተኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባዔ ኢትዮጵያ በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ስኬታማ ሥራዎችን ማከናወኗን የመንግሥት ኮሙኒኬሸን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሣ ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሀገራቱን የፖለቲካና የባህል ዲፕሎማሲ በኢኮኖሚው መስክ ማጠናከር እንደሚገባ የጋራ አቋም አንጸባርቀዋልም ብለዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሸን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሣ፤ በማብራሪያቸው የሩስያ-አፍሪካ የኢኮኖሚና የሰብዓዊነት ጉባዔ ኢትዮጵያ በልማት ሥራዎች ያስመዘገበቻቸውን ተጨባጭ ውጤቶች ያስተዋወቀችበት መሆኑንም አንስተዋል።
አፍሪካውያን በምግብ ራሳቸውን ለመቻል የሚያደርጉትን ጥረት ሩሲያ በቴክኖሎጂ ግብዓት እንድታግዝ ጥሪ ያቀረበችበትና የዘርፉ ተቋማት የሁለትዮሽ ስምምነቶችን የተፈራረሙበት ነው ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ በሩሲያ ቆይታው ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ስኬታማ ውይይት ማድረጉንና ወደ ተግባር የሚቀየሩ ስምምነቶችን መፈራረሙንም ጠቅሰዋል።
በሁለቱ መሪዎች ውይይት ኢትዮጵያ በተለይም በምግብ ራሷን ለመቻል በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ተምሳሌታዊ ተግባር እያከናወነች መሆኑም ተነስቷል ብለዋል።
ለ125 ዓመታት የዘለቀውን የሁለቱን አገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት በኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መስኮች ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችሉ ጉዳዮችም የውይይቱ አካል ነበሩ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በልማት መስክ በተለይም በግብርናው ዘርፍ ላደረገችው ስኬታማ እንቅስቃሴ የሩስያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አድንቀዋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት ሩሲያ በቴክኖሎጂ፣ በኢንቨስትመንትና በግብዓት የመደገፍ ፍላጎት ያላት መሆኑን አረጋግጣለች።
በጉባዔው የኢትዮጵያን የተለያዩ ተቋማት የወከሉ አመራሮች ከሩሲያ አቻዎቻቸው ጋር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችሉ ውይይቶች ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።
ለአብነትም የሰላምና ፀጥታ፣ የቴክኖሎጂ፣ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ትብብርን ማጠናከር ስለሚቻልባቸው ጉዳዮች መምከራቸውን በመጠቆም።
የሁለቱን አገራት ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት በኢኮኖሚውም ከፍ ወዳለ ደረጃ ማሸጋገር የሚችሉ ስምምነቶች መፈረማቸውን ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ ያነሱት።
የንግድ ትስስራቸውን ለማጠናከር እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን መፍታት የሚያስችል የጉምሩክ አገልግሎት ትብብር፣ በኢትዮጵያ የባዮሎጂካል ሳይንስ ምርምር ማዕከል ለማቋቋም፣ የአየር ትራንስፖርት ትብብርና የኒዩክሌር ኃይልን ለሰላማዊ አገልግሎት ማዋል የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ስምምነት መደረጉንም ጠቅሰዋል።
በአፍሪካ የኢንዱስትሪ ሂደቶችን ለማጠናከር ሩሲያ እንድታግዝ ኢትዮጵያ ጥሪ ማቅረቧን አስታውሰው በአፍሪካና ሩሲያ መካከል ያለውን የንግድ ትስስር እንቅፋቶችን ለመፍታት በጋራ መስራት እንደሚገባ በጉባኤው ተመላክቷል ነው ያሉት።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም የነዳጅ ዋጋ መናርንና የግብርና ግብዓት ችግሮችን ለመፍታት ሩስያ ከአፍሪካ ጋር አበክራ እንድትሰራ ጥሪ መቅረቡን አንስተዋል።
አፍሪካ የተፈጥሮ ኃብቷን እሴት ጨምራ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የምታደርገውን ጥረት የሩሲያ እገዛ ወሳኝ መሆኑ መነሳቱን በማስታወስ ኢትዮጵያ ሦስተኛውን የሩሲያ አፍሪካ ጉባዔ ለማስተናገድ ጥያቄ ማቅረቧንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል።
ሁለተኛው የሩሲያ-አፍሪካ የኢኮኖሚና የሰብዓዊነት ጉባኤ ባሳለፍነው ሳምንት ሐምሌ 20 እና 21 ቀን 2015 ዓ.ም በሩሲያ ቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ መካሄዱ ይታወቃል።