በጆርዳን ለስራ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን መብት እንዲጠበቅ ከዮርዳኖስ መንግስት ጋር በጋራ እየተሰራ ነው -አምባሳደር ገበየሁ ጋንጋ - ኢዜአ አማርኛ
በጆርዳን ለስራ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን መብት እንዲጠበቅ ከዮርዳኖስ መንግስት ጋር በጋራ እየተሰራ ነው -አምባሳደር ገበየሁ ጋንጋ
አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 24/2015 (ኢዜአ)፦ በጆርዳን ለስራ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን መብት እንዲጠበቅ ከዮርዳኖስ መንግስት ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው፣ ኤዥያና ፓስፊክ ዳይሬክቶሬት ጄነራል አምባሳደር ገበየሁ ጋንጋ አስታወቁ፡፡
በአምባሳደር ገበየሁ ጋንጋ የተመራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የልዑካን ቡድን በዮርዳኖስ የስራ ጉብኝት እያካሄደ ነው ።
አምባሳደሩ ከዮርዳኖስ የስራ ሚኒስትር ዴኤታ ዋና ጸሃፊ ፋሩክ አል ሃዲዲ ጋር ባደረጉት ውይይትም በሁለቱ አገሮች የሰራተኛ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች መካከል የተፈረመው የስራ ስምምነት ጸድቆ ወደ ስራ እንዲገባ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል ።
በኢትዮጵያ በኩል ስምምነቱን ለማጽደቅ አስፈላጊ የቅድመ-ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን፣ በስምምነቱ መሰረት በጆርዳን ለስራ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያንን መብት እንዲጠበቅ ከዮርዳኖስ መንግስት ጋር በጋራ ለመስራት ና በአማን ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ የክብር ቆንስል የሚያደርገው እንቅስቃሴ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በቅንጅት መሰራት እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡
ዋና ጸሃፊ ፋሩክ አል ሃዲዲ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በጆርዳን በርካታ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች እንደሚገኙ እና ይኸም በአገሪቱ ካለው የቤት ሰራተኛ ስምሪት ገበያ ውስጥ 80% እንደሚሆን ጠቅሰዋል፤ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች በዮርዳኖሳዊያን ዘንድ ተፈላጊ መሆናቸውን ጠቅሰው የአሁኑን ስምምነት በማስከተልም የኢትዮጵያን ፕሮፌሽናል እና መለስተኛ ባለሞያዎች ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በጆርዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን መብት እንዲከበርም የአገራቸው መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡
የልዑካን ቡድኑ በዮርዳኖስ ቆይታው በአማን ከተማ ከሚገኘው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ቆንስላ ጋር በመገናኘት የክብር ቆንስላ ጽህፈት ቤቱ ለዜጎች በመስጠት ላይ ባለው አገልግሎት ዙሪያ በተካሄደው ውይይት የጽህፈትር ቤቱ ስራ ቀልጣፋና ለዜጎች የበለጠ ተደራሽ እንዲሆን የመፍትሄ ሃሳቦች መቀመጣቸውን ተጠቅሷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በአሰሪዎቻቸው የተለያየ ችግር አጋጥሟቸው የቆንስላው ባዘጋጀው መጠለያ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በመጎብኘት ባጋጠማቸው ችግር ዙሪያ ውይይት መካሄዱንም ተገልጿል።
በዚህም ወደ አገራቸው ለመመለስ ፍላጎታቸውን በመግለጻቸው ከዮርዳኖስ የስራ ሚኒስቴር ጋር በጉዳዩ ላይ በመወያየት ዜጎች ጥቅማቸው ተከብሮ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ከመግባባት ላይ መደረሱ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
በቅርቡ በሁለቱ አገሮች የሥራ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች መካከል የተፈረመውን የስራ ስምሪት ስምምነት ወደ ስራ ለማስገባት በሁለቱም ወገኖች መካከል ጠንካራ ፍላጎት እንዳለ ለመገንዘንብ መቻሉም ነው የተመላከተው፡፡
በቀጣይም ስምምነቱ በሁለቱ አገሮች እንዲጸድቅና በስምምነቱ መሰረት የሚቋቋመው የጋራ ኮሚቴ ለስራ የሚሰማሩ ዜጎችን የሚያጋጥማውን ችግር ለመፍታት ቁልፍ መሳሪያ በመሆኑ ኮሚቴው እንዲመሰረት ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ጋር ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ግንዛቤ መወሰዱ ተመላክቷል፡፡