የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማቃለልና አገልግሎት አሰጣጡን በማቀላጠፍ አበረታች ማሻሻያ አድርጓል - የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማቃለልና አገልግሎት አሰጣጡን በማቀላጠፍ አበረታች ማሻሻያ አድርጓል - የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 24/2015(ኢዜአ) ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማቃለልና አገልግሎት አሰጣጡን በማቀላጠፍ አበረታች ማሻሻያ ማድረጉን የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ገለፀ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በተሻሻለው በአዋጅ ቁጥር 1142/2011 መሠረት የተቋቋመና ዋና ዓላማው በሕግ የተደነገጉ የዜጎች መብቶችና ጥቅሞች በአስፈጻሚው አካላት መከበራቸውን በማረጋገጥ የሕግ የበላይነትን መሠረት ያደረገ ጥራት፣ ግልጽነት ያለው መልካም አስተዳደር ማስፈን ነው።
ተቋሙ በ2015 በጀት ዓመት በ52 ጉዳዮች 164 ተቋማት ላይ ቁጥጥር ለማድረግ አቅዶ በ47 ጉዳዮች 164 ተቋማት ላይ ቁጥጥር ማድረጉን በዓመታዊ ሪፖርቱ ላይ አመላክቷል።
ተቋሙ የቁጥጥርና የክትትል ሥራ ከሰራባቸው ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት አንዱ ሲሆን ድርጅቱ የታየበትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የመፍትሄ ኃሳብ አቅርቦለት ነበር።
የቀረበለትን የመፍትሄ ሃሳብ ተከትሎ በ2014/15 ዓ.ም ተቋሙ ምን ያኸል አሻሽሏል የሚለውን ለመቃኘት የቁጥጥርና የክትትል ሥራው መከናወኑን በኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የአስተዳደር በደል መከላከል ዳይሬክተር አዳነ በላይ ለኢዜአ ገልጸዋል።
የቁጥጥር ሥራው የመስክ ምልከታን ጨምሮ የመሥሪያ ቤቱን የበላይ አመራሮችን፣ ፈጻሚ ባለሙያዎችን፣ ተገልጋዮች ማነጋገርና እንዲሁም ሰነዶችን የመፈተሽ ሥራ ማካተቱን ተናግረዋል።
ተቋሙ ባካሄደው የቁጥጥር ሥራ የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት የተስተዋሉ የመልካም አስተዳደርና የሥራ አፈጻጸም ክፍተቶች በ79 ነጥብ 1 በመቶ መሻሻል አሳይቷል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም እንዲሻሻሉ ካመላከታቸው ነጥቦች መካከል ሸገርና አንበሳ አውቶቡስ ድርጅቶች ወደ አንድ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል።
ይህም ደግሞ በተለይም መለዋወጫ በማጣት ቆመው የነበሩ አውቶቡሶች ወደ ሥራ እንዲገቡ ማስቻሉን አንስተዋል።
በሌላ በኩል አንድ የሠራተኛ ማኅበር መቋቋም መቻሉ ሠራተኛውን በሙያ የማብቃትና በደረጃ የማሳደግ እንዲሁም የተርሚናል ሥራዎችን በተገቢው ሁኔታ ማከናወን ማሻሻያ ከተደረጉባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት የቴክኒክና ግብዓት ዘርፍ አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አዳነ አብደታ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በዓመት ሁለት ጊዜ የቁጥጥርና ክትትል ሥራ ተቋሙ ላይ በማካሄድ በጠንካራና ደካማ ጎን ሪፖርት ማድረጉን ገልፀዋል።
በሪፖርቱም በዋናነት በመለዋወጫ ምክንያት ከሥራ ውጭ የነበሩ አውቶቡሶች ወደ ሥራ እንዲገቡ፣ የሥምሪት ክፍተቶችን፣ የሠራተኛ ማኅበር ውህደትን፣ የበጀት ድጎማ ማስተካከያዎችን እንዲሁም በውስጥ ሠራተኞች የሚያነሷቸውን የተለያዩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም መቅረባቸውንና ምላሽ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት የየካ ቅርንጫፍ የቴክኒክና ግብዓት አቅርቦት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኢንጂነር በለጠ ግርማ በበኩላቸው፤ ተቋሙ በተለይም የአውቶቡስ ጥገና ሥራዎችን ከቢሾፍቱ አውቶቡስ ማምረቻ አገልግሎት ድርጅት ጋር በጋራ በመሥራት አውቶቡሶቹ ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የሰለጠኑ የቴክኒክ ባለሙያዎች፣ የተደራጁ የጋራዥ አገልግሎት መስጫ ሥፍራዎች እንዲሁም የቴክኒክ ማንዋሎችን በማደራጀት በሪፎርም ሥራው ቀሪ ተበላሽተው የቆሙ አውቶቡሶችን በቀጣይ ሁለት ወራት ውስጥ ወደ ሥራ ለማስገባት እየሰሩ መሆኑንም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ልዩ ሪፖርት በተቋማት የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሻሻል በመገናኛ ብዙኃን በማጋለጥ፣ እንዲሁም በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ እያከናወነ መሆኑን መግለጹ ይታወቃል።