ተቋማት በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም የጀመሯቸውን ስራዎች አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል-የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አወል አርባ - ኢዜአ አማርኛ
ተቋማት በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም የጀመሯቸውን ስራዎች አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል-የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አወል አርባ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 23/2015 (ኢዜአ) ፡- ተቋማት በአፋር ክልል በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መልሶ ለማቋቋም የጀመሯቸውን ስራዎች አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አወል አርባ ጥሪ አቀረቡ፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በአፋር ክልል ካሳጊታ ከተማ በጦርነቱ የወደሙ አስር መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አወል አርባ በተገኙበት ዛሬ አስረክበዋል።
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በዚሁ ጊዜ፤ የካሳጊታ ከተማ በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባት ተናግረዋል።
በዚህም ነዋሪዎቹ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠው መቆየታቸውን ጠቁመው፤ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ አካባቢውን መልሶ ለመገንባት አብነት የሚሆን ስራ ማከናወናቸውን አንስተዋል፡፡
ሌሎች ተቋማትም የፕላንና ልማት ሚኒስቴርንና ተጠሪ ተቋማቱን ፈለግ በመከተል የመልሶ ማቋቋሙ ስራ ላይ አሻራቸውን እንዲያኖሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የቤቶቹ ግንባታ ከቤትም በላይ ለአፋር ህዝብ የተበረከተ የአብሮነት ሀውልት መሆኑንም ነው ርዕሰ-መስተዳድሩ ያብራሩት።
ተቋማት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚያከናውኗቸው ስራዎች ዜጎችን በመደገፍ በኩል ሚናቸው የጎላ መሆኑን ጠቁመው፤ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ በጋራ በመሆን ያከናወኑት ስራ አብነት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ጥሩማር አባተ ካሳጊታ በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች መካከል አንዷ መሆኗን ጠቁመው፤ በቀጣይም የከተማዋ ነዋሪዎችን በዘላቂነት ማቋቋም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም መላ ኢትዮጵያውያን ካሳጊታን መልሶ በመገንባት አሻራቸውን እንዲያኖሩ ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በከር ሻሌ በበኩላቸው በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ የመገንባቱ ስራ የሁሉንም ዜጋ ትብብር እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።