ተመራቂ ተማሪዎች ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ውስጥ ችግር ፈቺ ዜጋ ለመሆን በየጊዜው ራሳቸውን ማብቃት ይጠበቅባቸዋል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ተመራቂ ተማሪዎች ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ውስጥ ችግር ፈቺ ዜጋ ለመሆን በየጊዜው ራሳቸውን ማብቃት ይጠበቅባቸዋል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 23/2015 (ኢዜአ) ፦ ተመራቂ ተማሪዎች ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ውስጥ ችግር ፈቺ ዜጋ ለመሆን በየጊዜው ራሳቸውን ማብቃትና ማዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ በስሩ በሚገኙ በስምንት ኮሌጆች እና በስድስት ፓሊ ቴክኒክ ኮሌጆች በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 6 ሺህ 244 ሰልጣኞችን አስመርቋል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለተማራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ተወዳዳሪ የሰው ሃይል በማፍራት ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ትልቅ ድርሻ አላቸው ብለዋል።
በተለይ የኢንዱስትሪዎችና ኢንተርፕራይዞች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በኩል ጉልህ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት የምትፈልገው ችግር ፈቺ ትውልድ ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ ተመራቂዎቹ ዘመኑን በዋጀ አግባብ የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት እንዲሰሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመሆኑም ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ውስጥ የህዝብን ችግር ለመፍታት በርትቶ መስራት ይገባል ነው ያሉት።
የዛሬ ተመራቂዎች አሁን በደረሱበት ስኬት ብቻ ሳይወሰኑ ዘመኑ የደረሰበትን እውቀት፣ ቴክኖሎጂና ዘመናዊ አሰራር ጋር አብሮ ለመሄድ በየጊዜው ትምህርታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ የትምህርትና ስልጠና ተቋማቱ በዋናነት ለኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚውሉ ብቁ የሰው ሃይል በማፍራት ትልቅ ሚና እንዳለቸው ገልጸዋል።
ተቋማቱ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት ተልዕኳቸውን ውጤታማ ለማድረግ ከአደረጃጀት ጀምሮ የአሰራረ ማስተካከያ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል
ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራት ሰላማዊት ኃይሌ በስልጠናው ባገኘችው ክህሎትና እውቀት ህዝብን ለማገልግል ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች፡፡
ጌታቸው ሚቻ እና ብርሃኑ እሸቱ በበኩላቸው በቆይታቸው ባገኙት ክህሎት የራሳቸውን ስራ ፈጥረው የመሰማራት እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ተመራቂዎች ስራ መፈለግ ላይ ሳይሆን መፍጠር ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸውም ነው ያነሱት፡፡