የፕላንና ልማት ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት በአፋር ክልል ካሳጊታ ከተማ በጦርነቱ የወደሙ አስር መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ለነዋሪዎች አስረከቡ - ኢዜአ አማርኛ
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት በአፋር ክልል ካሳጊታ ከተማ በጦርነቱ የወደሙ አስር መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ለነዋሪዎች አስረከቡ
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 23/2015 (ኢዜአ) ፦ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት በአፋር ክልል ካሳጊታ ከተማ በጦርነቱ የወደሙ አስር መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ለነዋሪዎች አስረክበዋል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጥሩማር አባተ እና የተጠሪ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች የመኖሪያ ቤቶቹን የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳደር አወል አርባ በተገኙበት ለነዋሪዎቹ አስረክበዋል።
የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አወል አርባ፤ የካሳጊታ ከተማ በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባት እና በዚህም ነዋሪዎቹ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠው መቆየታቸውን ጠቁመዋል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን አካባቢውን መልሶ ለመገንባት አብነት የሚሆን ስራ ማከናወናቸውን ርዕሰ-መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡
የቤቶቹ ግንባታ ከቤትም በላይ ለአፋር ህዝብ የተበረከተ የአብሮነት ሀውልት መሆኑንም ነው ያብራሩት።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጥሩማር አባተ ካሳጊታ በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች መካከል አንዷ መሆኗን ጠቁመው፤ በቀጣይም የከተማዋ ነዋሪዎችን በዘላቂነት ማቋቋም ይገባል ብለዋል፡፡
በመሆኑም መላ ኢትዮጵያውያን ካሳጊታን መልሶ በመገንባት አሻራቸውን እንዲያኖሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በከር ሻሌ በአፋር፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ የመገንባቱ ስራ የሁሉንም ዜጋ ትብብር እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።