የኢትዮጵያ እና የሞሮኮ ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነት በውጤታማነቱ ቀጥሏል - በኢትዮጵያ የሞሮኮ አምባሳደር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እና የሞሮኮ ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነት በውጤታማነቱ ቀጥሏል - በኢትዮጵያ የሞሮኮ አምባሳደር
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 23/2015 (ኢዜአ) :- የኢትዮጵያ እና የሞሮኮ ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነት በውጤታማነቱ መቀጠሉን በኢትዮጵያ የሞሮኮ አምባሳደር ኔዛ አሎዩ ምሃምዲ ገለጹ።
የኢትዮጵያ እና የሞሮኮን ግንኙነትን በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ የሞሮኮ አምባሳደር ኔዛ አሎዩ ምሃምዲ፤ የሁለቱ አገሮች ዘርፈ ብዙ የትብብር መስኮች በውጤታማነት መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
የሞሮኮው ንጉስ መሃመድ ስድስተኛ እ.ኤ.አ በ2016 በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድርጋቸውን ተከትሎ አገራቱ 16 የአጋርነት ሥምምነቶችን በመፈራረም ለተግባራዊነቱ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም የኢትዮጵያና ሞሮኮ ወዳጅነትና የትብብር ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገሩን አምባሳደሯ ተናግረዋል።
በተለይም በግብርና፣ በትምህርት፣ በኢንቨስትመንትና በኢከኖሚ ትብብር መስኮች አገራቱ በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም በእነዚህና በሌሎች መስኮች ሞሮኮ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የትብብር ግንኙነት አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
የኢትዮጵያ እና የሞሮኮ ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነት በተሳካ መልኩ በውጤታማነቱ ቀጥሏል ያሉት አምባሰደሯ፤ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማጠናከር በባንክና ሌሎችም መስኮች በትብብር እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ እና የሞሮኮ ስትራቴጂክ አጋርነት መጠናከሩን የገለጹት አምባሳደር ኔዛ አሎዩ፤ ከግብርና፣ ንግድና ኢንቨስትመንት በተጨማሪ በስፖርት ዘርፍም በጋራ እንሰራለን ብለዋል።
በዓለም ስመ ጥር የሆኑ አትሌቶች መፍለቂያ ከሆነችው ኢትዮጵያ፤ ሞሮኮ ልምዶችን መጋራት ትሻለች ያሉት አምባሳደሯ፤ ሞሮኮም በእግር ኳስ የካበተ ልምዷን ለኢትዮጵያ ታጋራለች ሲሉ ተናግረዋል።
በቀጣይ ይካሄዳል ተብሎ የሚታሰበው የኢትዮ-ሞሮኮ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ከማጠናከር ባለፈ የሥምምነት ማዕቀፎችን አፈፃፀም የሚገመግሙበት ይሆናል ተብሏል።
የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቅርቡ በኬንያ ከተካሄደው 43ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈፃሚዎች መደበኛ ስብሰባ ጎን ለጎን በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ይታወሳል።