በተለያዩ ዓለም አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው እድገት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ይሰራል - የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር - ኢዜአ አማርኛ
በተለያዩ ዓለም አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው እድገት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ይሰራል - የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 22/2015(ኢዜአ)፡- በተለያዩ ዓለም አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው እድገት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ በትኩረት እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር ገለጸ።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር እንደ አዲስ ተደራጅቶ ወደ ሥራ መግባቱን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።
ማኅበሩ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ አካሂዶ በነበረው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አዳዲስ አመራሮችን መምረጡንም ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር ሰብሳቢ ቅድስት ልዑልሰገድ በዚሁ ጊዜ ማኅበሩ የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማጠናከር የሚያስችል አዲስ አደረጃጀት ተፈጥሮ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።
ይህንንም ተከትሎ ማኅበሩ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ባላቸው እውቀት፣ ገንዘብና ልምድ የአገራቸውን እድገትና ብልጽግና እንዲደግፉ በትኩረት እንደሚሰራ ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ ዕድገት በቴክኖሎጂ የተቃኘ እንዲሆንና በዚህም የዳያስፖራው ተሳትፎ ይበልጥ እንዲጠናከር ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች እንዲቀጥሉ አጽንጾት እንደሚሰጠው ተናግረዋል።
በአዲስ መልክ የተደራጀው ማኅበሩ ለአገር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ውጤታማ ይሆን ዘንድ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የማኅበሩ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ደመቀ ነጋሳ በበኩላቸው "በየትኛው ዓለም አገራት የምንገኝ ዳያስፖራዎች አገር ለማገዝ ከእኛ ሚጠበቅብንን አገራዊ አደራ መወጣት አለብን" ብለዋል።
ኢትዮጵያ በየጊዜው ሚገጥማትን ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ዳያስፖራው አሁንም ተሳትፎው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተዋል።
በአገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች በሚካሄዱት የልማት ፕሮጀክቶች ዳያስፖራው ተሳትፎውን በማጎልበት እራሱንና አገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ጥረቱን ማጠናከር እንዳለበትም እንዲሁ።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር በአዲስ መልክ መደራጀቱ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ተሳትፎ በአገራቸው ጉዳይ የበለጠ ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ያግዛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር አሁን ላይ 10 ሺህ የሚጠጉ አባላት እንዳሉት ከማኅበሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።